“የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ ፈተና ወደ መፈተኛ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሄዱ የአካባቢያቸው አምባሳደር መኾን አለባቸው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

60

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣይ ከሐምሌ 19 እስከ 30 /2015 ዓ.ም ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በቂ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መረጃ ፈተናው በታቀደለት አግባብና ጊዜ፣ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ለዚህም በክልል ደረጃ የጸጥታ መዋቅሩንና የትራንስፖርት ዘርፉን ያካተተ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር በውጤታማነት ለመምራት ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል ነው ያሉት።

በክልሉ በ572 ትምህርት ቤቶች 215 ሺህ 770 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ ተመዝግበዋል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በስኬት እንዲከናወን ባለፈው ዓመት የታዩ ጉድለቶችን በማረም፣ ለተሻለ ውጤታማ የፈተና ሂደት እየተገመገመ በአግባቡ እየተመራ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ዩኒቨርሲቲዎች ሲገቡ የአካባቢያቸው አምባሳደር መኾን እንደሚገባቸውም አደራ ብለዋል ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ እየሩስ መንግሥቱ።

የሚወስዱት ፈተና፣ የፈተና ሂደቱና የፈተናው ውጤት የተማሪዎች ብቻ አይደለምና ፈተናውን በሚያስመሰግን መልኩ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው መረዳት ይገባቸዋል ብለዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎች የወላጆቻቸውን፣ የመምህሮቻቸውንና የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ በሚመጥን አግባብ በሥነ-ምግባር ጨዋነት የተዘጋጀላቸውን ፈተና መውሰድ እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

ለዓመታት የተማሩትን ትምህርትና የወሰዱትን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ ዝግጅታቸውን በኀላፊነት ለጥሩ ውጤት ማብቃት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።

የሚያስመዘግቡት ውጤት የተማሪዎቹ ብቻ መገለጫ አይደለምና ለሀገራቸው ክብር መጠንቀቅ ይገባል ነው ያሉት።

የፈተና ሂደቱ በጥንቃቄ እና በሰላም እንዲከናወን በመንግሥትና በባለድርሻ አካላት በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ተማሪዎችም የፈተና ሥርዓቱንና ሕግን አክብረው ፈተናውን እንዲወስዱ አደራ ብለዋል።

ዘጋቢ፦ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
Next articleአዲሱ ክልል” የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” በሚል ስያሜ እንዲዳራጅ ተወሰነ።