“በክልሉ ከ32 በላይ የቱሪስት መዳረሻ ቅርሶች ጥገና ላይ ናቸው” ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ

40

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና መልክዓምድራዊ መስህቦች በአማራ ክልል ውስጥ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች መካከል በርካቶቹ የዓለም ሕዝብ ሃብት እና ንብረት ወደ መኾን ተሸጋግረው በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም ዩኒስኮ ተመዝግበዋል፡፡ መስፈርቱን የሚያሟሉትንም ለማስመዝገብም በእንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት በነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ክስተት በፊት በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ከኾኑ ግንባር ቀደም አካባቢዎች አንዱ የአማራ ክልል ነበር፡፡ በክልሉ ከሚገኙ በርካታ የቱሪስት የስበት ማዕከላት መካከል የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን ተከትሎ የጎብኝዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል፡፡ በበርካታ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሕይዎታቸው የተመሠረተው በቱሪዝም ከሚገኝ ገቢ ላይ ነው፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቋረጡን ተከትሎ ቅርሶች እና የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡

የቱሪዝም እንቅስቃሴው መልሶ እንዲያገግም ከሚደረገው ዙሪያ መለስ ዘመቻ ባሻገር የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አበበ እምቢያለ ገልጸዋል፡፡ የቅርስ ጥገና ሥራዎቹ በክልሉ መንግሥት መደበኛ በጀት፣ በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት የሚካሄድ ነው ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት 17 ሚሊዮን ብር ለቅርስ ጥገና በጅቷል ያሉት አቶ አበበ በ32 ቅርሶች ላይ ጥገና እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ ለቅርስ ጥገና መንግሥት 60 በመቶውን ድርሻ ይሸፍናል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው 40 በመቶው ደግሞ በሕዝብ የሚሸፈን ይኾናል ነው ያሉት፡፡ የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን 35 ሚሊዮን ብር በጀት እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ምክንያት ወረራ እና ዝርፊያ የተፈጸመበት የደሴ ሙዚየም ለጥገና እና መልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር ስምምነት መደረጉን አቶ አበበ አንስተዋል፡፡ የብሪቲሽ ካውንስል በመደበው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ጥገና እየተደረገለት ነው ተብሏል፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ ጥገናም በፈረንሳይ መንግሥት የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ጥገና እየተደረገለት ነው፡፡

የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ቀደመ ደረጃው ለመመለስ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት አቶ አበበ ከጥገና እና ከአቅም ግንባታ ሥራዎች በተጨማሪ የክልሉ መንግሥት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የአማራ ሕዝብ ሙዚየም ግንባታ ተጀምሯል ተብሏል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገነባው የአማራ ሕዝብ ሙዚየም የግንባታ ሥራውን የአማራ ሕንጻ ሥራዎች ድርጅት እያከናወነው መኾኑን አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ የሙዚየም ግንባታው ሲጠናቀቅ የክልሉን ባሕል፣ ትውፊት፣ ቅርስ፣ ማንነት እና እሴት ሙሉ በሙሉ የሚገልጽ ከመኾኑም ባሻገር አንዱ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ይኾናልም ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ዛሬ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።
Next articleበበጀት ዓመቱ 42 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ከ4 መቶ በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የሰሜን ሸዋ ዞን አስታወቀ።