
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የስጋትና ያለመተማመን መነሻ ከመኾን ይልቅ የትብብርና የዜጎችን የመልማት ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች መሆኗን የስትራቴጃዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የስትራቴጃዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ብዙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሉ። ኢትዮጵያ በየጊዜው በውኃ ዙሪያ ምክክሮችን በማዘጋጀት የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን እየሠራች ነው። እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች የስጋትና ያለመተማመን መነሻ ከመሆን ይልቅ የትብብርና የዜጎችን የመልማት ጥያቄዎች እንዲመልሱ ለማድረግ ጠንካራ ውይይቶችንና ምክክሮችን እያዘጋጀች ነው።
አፍሪካውያን ሀብታቸውን መጠቀም አለባቸው የሚለውን ሀሳብን በማንሳት ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች ያሉት ኃላፊው፤ የአፍሪካ ችግርን በአፍሪካውያን የሚለውንም መንፈስ በመያዝ ተግባራዊ በማድረግ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት ኾናለች ብለዋል።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ከግጭት ይልቅ የመተባበሪያ ምክንያት መሆን አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ወንዞቹ መተባበሪያ፣ አብሮ ማደጊያ፣ የመነጋገሪያና እንደ አንድ መሰለፊያ እንጂ የግጭት መነሻ ምክንያት መኾን የለባቸውም።
የልማት ጥያቄያችንን የምንመልስበት፣ የአየር ንብረት ለውጥን የምንመክትበት መሣሪያ እንጂ የግጭትና የኢ-ፍትሐዊ አጠቃቀም ተምሳሌትና የቅኝ ግዛት ውሎችን በአፍሪካውያን ላይ የሚጫንበት አይነት አግባብ መኖር የለበትም በሚለው ዙሪያ የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትም የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ሲሉ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ የሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ከቀጠናው ውጭ ያሉ ሀገራትን ለማሳተፍ የሚደረጉ ጥረቶች ተገቢ እንዳልሆኑ የተፋሰሱ ሀገራት ያሰመሩበት ጉዳይ መሆኑን አቶ ጃፋር ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ብዛትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቃች ነው። ይህን ኢ-ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም መፍታት የሚቻለው ያላትን ሀብት በራሷ መጠቀም ስትችል መሆኑን አፍሪካውያን ያምናሉ። የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መከላከልና ልማትን በዘላቂነት ለማስቀጠል አፍሪካ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን መጠቀም እንዳለባት የጋራ መግባባት መኖሩን ገልጸዋል።
የዓባይ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ስለ ቀጣናዊ ትስስርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችን በተለይ የዓባይ ውሃን በጋራ መጠቀም በሚቻልበት ዙሪያ በየዓመቱ ይወያያሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አፍሪካውያን ሀብታቸውን በራሳቸው መጠቀም እንዳይችሉና ልማታቸውን እንዳያሳድጉ የተለያዩ የቅኝ ግዛት ውሎች፣ ገደቦችና ጫና የሚደረግበትን አግባብ በጋራ መመከት ላይ በመምከር እየሠሩ ነው። ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችን ለጋራ ብልጽግና ለመጠቀም ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍሪካውያን ሀብታቸውን በራሳቸው አቅምና ያለ ማንም ጣልቃገብነት መጠቀም እንዲችሉ መነጋገር አለባቸው ብለውም፤ አፍሪካ ሀብቷን ለመጠቀም የእኛን ይሁንታ ማግኘት አለባት ከሚል ያረጀ ያፈጀ ከቅኝ አገዛዝ አመለካከት ወጥተን በራስ ፈቃድ መሥራት አለብን ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላውን ሳይጎዱ በፍትሐዊነት መጠቀም የሚችሉበትን አግባብ መቀየስ ተገቢ ነው። በተለይ የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ ያላቸው አንዳንድ አገራትን የሚያርጉትን ያልተገባ ተፅዕኖ ለማስቆም በጋራ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው በተለይም ከአፍሪካ ውጭ ሌሎች ሀገራት የአፍሪካውያንን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ፍላጎትን በዲፕሎማሲ ተፅዕኖ እንዳይጠቀሙ የሚያደርጉትን አካሄድ በማውገዝ አፍሪካውያን ሀብታቸውን በጋራ በመጠቀም ትስስራቸውን የማጠናከር ሥራ እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!