
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 04/2012ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶችና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በባሕር ዳር ዛሬ ታህሳስ 04 ቀን 2012ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ውይይት አድርጓል።
ከ10 ወራት በፊት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ቅራኔዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በዓዋጅ ቁጥር 1102/2011 ዓ.ም የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወሳል። ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚሠራ ነው። ኮሚሽኑ ዛሬ “ሀገሪቱን ለዕርቅ ያደረሳት ችግር ምንድን ነው? መፍትሔውስ ምን ይሆን?” ሲል በባሕር ዳር ከሰዓት በፊት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከሰዓት በኋላ ከነዋሪዎች ጋር መክሯል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም “ሀገሪቱ ሰው ናፍቋታል፤ ሰው ያስፈልገናል፤ ለሀገሪቱ መጸለይ፣ መልካም መሥራትና በጋራ መቆም ያስፈልጋል። ኮሚሽኑ የያዘው ኃላፊነት ትልቅና ሰናይ ነው” ብለዋል። ውይይቱ ጥልቀት ያለው መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል። ሠላም የሁሉም ለሁሉም ስለሆነ ሁሉም መሥራት መቻል እንደሚገባውም አሳስበዋል። “ከዚህ ቀደም የተዘራው የዘር ጥላቻ ሀገሪቷን ችግር ውስጥ ከትቷታል፣ ይህ ዘር በጋራ መታጨድ አለበት” ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።
“ዕርቁ ከማን ጋር ነው የሚደረገው? ሕዝብና ሕዝብስ ተጣልቷል ወይ? ኮሚሽኑ እስካሁን እነማንን አስታረቀ?” ሲሉም ነዋሪዎቹ ኮሚሽኑን ጠይቀዋል። መንግሥት በተለያዬ አጋጣሚ የሚያደርገውን የገንዘብ ፈሰስ ሰው ግንባታ ላይ ማድረግ እንዳለበትም መክረዋል። ኮሚሽኑም ሆነ መንግሥት እሳት ከማጥፋት ሥሩን መፈለግና መንቀል እንደሚገባቸውም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል። “የኢትዮጵያውያን ታሪክ ይቅርታ አድርገው ይቅርታ መቀበል ነው” ያሉት ነዋሪዎቹ የሃይማኖት አባቶች ይቅርታና ፍቅር ከሌለ የሰማይ ቤት ዝግ እንደሆነ ማስተማር እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የኢትዮጵያውያን የሠላም መንገድ የተበላሸው የት ላይ ነው? የሚለውን መለዬት እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አንስተዋል። የተዛባው አስተሳሰብ ከአዕምሮ ሳይወጣ አስቀድሞ ማጥፋት እንደሚገባና ለሕዝቡም ብልህ እረኛ እንደሚያስፈልግም ነው በውይይታቸው ያነሱት።
“ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሳቀሱ ስንቅ ተቋጥሮላቸው፣ እግራቸውን ታጥበው መኝታ ተዘጋጅቶላቸው በሠላም የሚሸኛኙ ናቸው” ያሉት ነዋሪዎቹ ሕዘብና ሕዝብ ስላልተጣላ “የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ የተጣሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና እናውቅልሀለን ባዮች ያስታርቅ” ነው ያሉት። “ኮሚሽኑ መቀሌ እና ባሕር ዳር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞችንና ሌሎችንም ፖለቲከኞች አገናኝቶ ማስታረቅ ከቻለ ችግሩ በአንድ ቀን ይፈታል፤ ጊዜያችሁንም ፖለቲከኞች ላይ ተጠቀሙት ነው” ብለዋል። “ለዕርቅ የሚያስፈልገውን ድርሻ መለዬት ከቻላችሁ ለማገዝ ዝግጁ ነን” ነውም ያሉት ነዋሪዎቹ። ጨዋነት የሌለው ሕዝብ ስልጣኔ እንደሚበላው ያነሱት ነዋሪዎቹ መሪዎች ብልኃት የተመላበትና ሀገርን ያስቀደመ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
“ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዕርቅ የፈጠረች ሀገር ለምን የራሷን ሠላም መጠበቅ አቃታት?” ያሉት ነዋሪዎቹ መደኃኒቷን ለመፈለግ በሽተዋን ማወቅ ተገቢ እንደሆም አመላክተዋል። መንግሥት ለሀገር ሠላም ስጋት የሆኑ ሰዎችን ከመንከባለብ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም ጠይቀዋል። ፖለቲካ አንዱ ችግር ቢሆንም ፖለቲካ ብቻ ለሀገሪቱ ችግር ስላልሆነ ሌሎች ችግሮች ላይም መሠራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። “መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅም አጥቷል፤ ሠላምን ለማምጣት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን እርስ በርስ አገናኝቶ ማወያዬት ያስፈልጋል” ብለዋል። ነዋሪዎቹ የኢትዮጵያን ሠላም ለማምጣት ከተፈለገ የተገነቡ የጥላቻ ሀውልቶች መፍረስ እንደሚኖርባቸው ጠይቀዋል።
በታሪክ ያልተፈጠረን ውሸት እውነት አስመስሎ ማቅረብ አብሮ ስለማያኖር የውሸቱ ሀውልቱ እንዲፈርስ አሳስበዋል። የሀገር ሠላም ለማምጣት የሃይማኖት አባቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች ጋር የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር እርስ በርስ መግባባት አለባቸውም ብለዋል። “ለሠላም ዋጋ መክፈል ያስገልጋል፣ መክፈልም አለብን። ክፉን በመልካም በመመለስ ሳትጎል የተረከብናትን ሀገር ሳትጎድል ማስረከብ አለብን” ብለዋል።
የኮሚሽኑ አባላት ደግሞ ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ “የዕርቀ ሠላሙን ዓላማ ስንረዳ፣ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎች ስናይ፣ እውነታዎችን እና አሰራሮችን ለማወቅ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር ውይይት ስናደርግ ቆይተናል። ዝም ብለን የተጣሉ ሰዎችን ፍለጋ ብቻ አልሄድነም” ብለዋል። ከመገናኛ ብዙኃን ጋር እንደተወያዩና “አስታራቂ ጋዜጠኛ” የሚል ፎረም እንዳቋቋሙና ብሔራዊ የጸሎት ቀን እንዳሳወጁም ገልፀዋል። ከተለያዩ የፖለቲካ አካላት ጋር እንደተወያዩ እና የፖለቲካ ፓሪቲዎችም ለዕርቅ ሠላም በራቸው ክፍት እንደሆነ መናገራቸውን አስታውቀዋል። አሁን ተግባራዊ የዕርቀ ሠላም ሂደት ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑም ገልፀዋል። የኮሚሽኑ ሰብሳቢ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ይህ የመጠላላት ዘመን እንደሚያልፍ ገልፀው “የአማራ ሕዝብ ታላቅነቱንና መልካምነቱን እንዳይረሳ” ሲሉ አሳስበዋል። “ሕዝቡ ፈተና የበዛበት ቢሆንም ሠርቶ ያደረ፣ መልካምነትን ያስተማረ በመሆኑ ይህን ታላቅነቱን እንዳይዘነጋ፤ ተስፋም እንዳይቆርጥ” ብለዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ