“ለ15ኛ ጊዜ ለሚዘጋጀው የአማራ ክልል የባሕልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቅቋል።” የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ

70

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት በየዓመቱ ክልል አቀፍ የባሕልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ሲዘጋጅ ቆይቷል። ባለፉት ዓመታት ግን በኮሮና ቫይረስና በሀገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል።

በዚህ ዓመት 15ኛውን ክልል አቀፍ የባህልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ሀምሌ 1-2/2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ለማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጣሂር ሙሃመድ አስታውቀዋል። ፌስቲቫሉ “ባሕላችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

ፌስቲቫሉ የልምድ መለዋወጫ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ፣ የአንድነት መፍጠሪያ እንዲሁም የችግሮች መፍቻ መንገዶች መኾናቸውን አቶ ጣሂር ገልጸዋል። ፌስቲቫሉን ለማዘጋጀት ቢሮው ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

አቶ ጣሂር በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት በፌስቲቫሉ በክልላችን ከሚገኙ ዞኖችና ከተማ አሥተዳደሮች የሚመጡ የባሕል ቡድኖች ይሳተፉበታል።

የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ክልሎች የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ እና የሁሉም ዞኖችና ከተማ አሥተዳደሮች ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሏል።

ከባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ያገኘነው እንደሚያሳየው በፌስቲቫሉ የሙዚቃ ውድድር፣ የስዕልና ቅርፃ ቅርፅ አውደ ርዕይ፣ የእደ-ጥበብ አውደ ርእይና ሌሎችም ዝግጅቶች ይቀርባሉ።

በክልሉ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የጥበብ ሰዎችም ዕውቅና እንደሚሰጥ አቶ ጣሂር ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፌዴሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ
Next articleየፌዴሬሽን ምክር ቤት የምርጫ ቦርድን ሪፖርት ማዳመጥ ጀመረ