
ደብረ ታቦር:ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የክልሉን የእንስሳት ሃብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ስልጠና በወረታ ከተማ እየተሰጠ ነው። ከሰሜን ወሎ፣ ዋግኽምራ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች የተወጣጡ የእንስሳት ሃብት ባለሙያዎች የስልጠናው ተካፋይ ናቸው።
በስልጠናው ላይ የተገኙት የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ነጋ ይስማው የተሻሉ ቴክኖሎጅዎችን እና አሠራሮችን በመተግበር የእንስሳትን ምርታማነት የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል። በእንስሳት ልማት ዘርፍ የተሰማራ ማንኛውም አካል ውጤታማ እንዲኾን ከተፈለገ ሳይንሳዊ ምርምር ተካሄዶባቸው የተቀረጹ ፓኬጆችን ተግባራዊ ማድረግ እና የተሻሉ አሠራሮችን መከተል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እየተሰጠ ያለው ስልጠና በክልሉ የተሻለ መጠን እና ጥራት ያለው የወተት፣ የሥጋ፣ የእንቁላል እና ሌሎችን የእንስሳት ተዋጽዖዎች ለማግኘት ያለመ ስለመኾኑም አቶ ነጋ ተናግረዋል። የክልሉን እምቅ የእንሳት ሃብት በመጠቀም ለሕዝቡ የተሻሻለ ሥርዓተ ምግብን ማረጋገጥ ግድ ይላል ብለዋል። በዝቅተኛ እና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችም የእንስሳት ተዋጽዖ ተጠቃሚ መኾን አለባቸው ነው ያሉት። ይህ እንዲኾን ደግሞ እንስሳትን በዘመናዊ መልኩ እና በብዛት በማርባት የዋጋውን መጠን ዝቅ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። የምርት መጠኑን በማሳደግ እና ወደ ዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማመንጨትም በትኩረት መሠራት እንዳለበት አንስተዋል።
የጽሕፈት ቤቱ መረጃ እንደሚያመለክተው የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት 24 ነጥብ 26 በመቶ የሚኾነውን ሀገራዊ ድርሻ ይሸፍናል።
➡ በክልሉ፦
👉 17 ሚሊዮን 300 ሺህ የዳልጋ ከብቶች፣
👉 10 ሚሊዮን 400 ሺህ በጎች፣
👉 7 ሚሊዮን 45 ሺህ ፍየሎች፣
👉 4 ሚሊዮን 400 ሺህ የጋማ ከብቶች፣
👉 44 ሽህ 774 ግመሎች፣
👉 19 ሚሊዮን 90 ሺህ ዶሮዎች፣
👉 1 ሚሊዮን 380 ሺህ ኅብረ ንብ እና
👉 በዓመት እስከ 40 ሺህ ቶን የዓሣ ምርት ከወንዝ እና ሐይቆቹ የሚገኝበት ክልል ነው።
የክልሉ የእንስሳት ሃብት ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና የሚጫዎት ቢኾንም ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ አለመሠራቱም ተገልጿል።
በስልጠና የሚገኘውን ዕውቀት እና ክህሎት ወደ ተግባር በማስገባት የእንስሳት ሃብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠሩም ሰልጣኞች ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!