“የደመወዝ ጉዳይ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ የሚታይ ይኾናል” የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ

205

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ጉባዔው በ2016 ሪቂቅ በጀት ላይ ተወያይቷል። በውይይቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የክልሎች የገቢ አቅም እያደገ መኾኑን ተናግረዋል። ክልሎች የበጀት አጠቃቀማቸውን መፈተሸ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የያዛቸው ሥራዎች ክልሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የልማት ፕሮጄክቶች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከሥራ ቅጥር ጋር በተያያዘ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ በፌዴራል መንግሥት የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ቁጥር ተቀንሷል፣ ይሄም የኾነው በጀትን ከውጤታማነት ጋር ለማስተሳሰር ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመንግሥት ተቀጣሪ ቁጥር ብዙ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ውጤታማ ለማድረግና ስኬታማ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ የመንግሥት ቅጥር አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል፡፡

የግል ዘርፉን አቅም በማሳደግ እና የቱሪዝም ዘርፉን በማስፋት የሥራ እድል እንዲፈጠርባቸው ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ መንግሥትም የግል ዘርፉን በመደገፍ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡ የሥራ እድል እንዲፈጠር መንግሥት ኀላፊነት ወስዶ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ለውጥ ላይ በውስን አደረጃጀት የላቀ ውጤት የማምጣት ሂደትን መሠረት ያደረገ ነውም ብለዋል፡፡

የደመወዝ ጉዳይ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ የሚታይ መኾኑንም አንሰተዋል፡፡ የማዳበሪያ ችግሩን ለመፍታት የግብርና ሚኒስቴር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ወደ ፊት ወቅቱን ጠብቆ ለማቅረብ ይሠራል ነው ያሉት፡፡

የማደበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ መንግሥት ከመጠባበቂያ በጀትም ጭምር በመመደብ ማስገባቱንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በምክር ቤቱ የጸደቁ ፕሮጄክቶች በጀት ተይዞላቸዋል” የገንዘብ ሚኒስተሩ አሕመድ ሽዴ
Next article“ትናንት የተሰጡት የሬሜዲያል ፕሮግራም ፈተናዎች ተሰርዘዋል” የትምህርት ሚኒስቴር