“በምክር ቤቱ የጸደቁ ፕሮጄክቶች በጀት ተይዞላቸዋል” የገንዘብ ሚኒስተሩ አሕመድ ሽዴ

45

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ጉባዔው በ2016 ዓ.ም ሪቂቅ በጀት ላይ ነው የተወያየው፡፡ በውይይቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የበጀት ድልድል የሚካሄደው የመሥሪያ ቤቶችን አቅምና አፈጻጸም በማየት እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት፡፡

የበጀት ድልድሉ ተገቢውን ፍተሻ በማድረግ የተመደበ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የዋጋ ንረቱ እንዳይሠፋ በተቻለ መጠን ቁጥጥር ይደረጋል፣ እድገትንም እናሰፋለን ብለዋል፡፡

የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የግሉን ዘርፍ ማስፋት ይገባልም ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ በሚቀጥለው ዓመት የተሻለ እንደምታድግ ተስፋዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ንረት እንዳይሰፋ ታቅዶ በጀት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ የተጀመሩ ልማቶችን ብቻ ለማስጨረስ ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ነባር ፕሮጄክቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በቅደም ተከተል ይፈጻማሉም ብለዋል፡፡

በምክር ቤቱ የጸደቁ ፕሮጄክቶች በጀት እንደተያዘላቸውም ገልጸዋል፡፡ የበጀት ክፍተቶችን እና ጥያቄዎችን ለመፍታት የመጠባበቂያ በጀት ከፍ ብሎ መያዙንም ተናግረዋል፡፡ በበጀት የተተከሉ ፕሮጄክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በአግባቡ ይስተናገዳሉ ነው ያሉት፡፡

የዋጋ ንረትን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በኑሮ ውድነቱ ተጎጂዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ጉዳዩን ለመፍታት የሲቪል ሰርቪስ ለውጥን ምክንያት በማድረግ አደረጃጀቶችን እንፈትሻለን ነው ያሉት፡፡

የእዳ የመክፈል አቅም ማደጉንም ተናግረዋል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት የሀገር ውስጥ ገቢ ማሳደግን ትኩረት አድርጎ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ለውጡ ስኬት እያመጣ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሥርዓተ ምግብ ችግር አኹንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ሀገራዊ አጀንዳ ነው” የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ.ር)
Next article“የደመወዝ ጉዳይ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ የሚታይ ይኾናል” የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ