
አዲስ አበባ: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃል ኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ የ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረውን የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም እና በኢትዮጵያ የሚተገበረውን የምግብና የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ትግበራ በማፋጠን ፤ መንግሥት አሁን በመታደግ ላይ ካለው በተጨማሪ 7 ሚሊዮን 852 ሺህ 216 ሕፃናትን በ15 ዓመታት በመታደግ ፤ ሙሉ ዕድገታቸውን እና ምርታማነታቸውን ለማረጋገጥ በ2007 ዓ.ም ቃል የተገባበት ስምምነት ነው።
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በምግብና ሥርዓተ ምግብ ትግበራ ማስፋፋት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ቢገኙም የሥርዓተ ምግብ ችግርን መፍታት አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው ሀገራዊ አጀንዳ እንደኾነ ገልጸዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ ተጽዕኖ፣ የምግብ ዋጋ ንረት፣ ድርቅና ከግጭት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ችግሮችን ማባባሳቸውን ገልጸዋል። በተለይም የነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ፤ ታዳጊዎችና ሕፃናትን ለከፋ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ችግር መጋለጣቸውን ነው የተናገሩት።
በመድረኩ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጅና የሰቆጣ ቃል ኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ዓመታዊ አፈፃፀምን በመገምገም፤ መልካም ተሞክሮዎችን በመለየት፤ በቀጣይ 2016 ዓ.ም ዓመታዊ ዕቅድ ዝግጅት ለግብዓትነት የሚጠቅም እንደኾነም ጠቁመዋል።
የቅንጅታዊ አሠራርን፣ የገንዘብና የሰው ኀይልን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ተግባራትን በመለየት በፌዴራልና ክልል ያሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አጋር ድርጅቶች በከፍተኛ ቁርጠኝነት በዕቅድ ውስጥ ተካተው እና ኹሉም ባለድርሻ አካላት የመንግሥትን ቁርጠኝነት በመጠቀም ትግበራውን ለማፋጠን የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!