
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡ በመደበኛ ጉባዔው የፌዴራል መንግሥት የ2016 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ እየተወያየ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጀቱን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል የሰላሙ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የሰላም ማዕከል እንደኾነች ቢነሳም አሁን ላይ ያን የሚያመላክት ሰላም በሀገሪቱ እንደሌለ አንስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም ከሌለ በጀቱ ልማትን ሊያሳካ አይችልም ነው ያሉት። ሰላምን ከጫፍ ጫፍ ለማስፈን ከማን ምን ይጠበቃል? የሚለውን በመለየት ቁጭ ብለን በመወያየት ሰላምን ካላጻናን በጀቱ ምንም ነው ብለዋል፡፡
የሕዝብና ቤት ቆጠራ በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሏል ያሉት አባላቱ ያን ታሳቢ ያደረገ ምን ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሙስናን ለመግታት እየሠራች ቢኾንም አሁንም ሕዝቡ በሙስና እየተሰቃየ ነውም ብለዋል፡፡ የመንግሥት በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የሚደረገው ቁጥጥር ምን እንደሚመስልም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል የመብራት እና የኔትወርክ አገልግሎት ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል። በአማራ ክልል የወረዳ ከተሞች ጭምር መብራት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ አሁንም በድንጋይ ወፍጮ የሚፈጩ ትኩረት ያልተሰጣቸው አካባቢዎች አሉ ነው ያሉት፡፡የበጀት አመዳደብ ኢ-ፍትሐዊነት መኖሩንም አንስተዋል፡፡
የመስተንግዶ በጀት በደሃ ሀገር በአላስፈላጊ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱም በአባላቱ ተነስቷል፡፡ የገንዝብ ሚኒስቴር ያለ አግባብ የሚባክን በጀትን ለመቆጣጠር ምን እየሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል፡፡
የሚመደቡ በጀቶች ለሚፈለገው ዓላማ እየተለቀቁ አለመኾናቸውም ተነስቷል፡፡
መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት ችግሮች እንዳሉበት ያነሱት የምክር ቤት አባላቱ በ2016 ዓ.ም መሰል ችግሮችን ለመፍታት ምን እንደታሰበ እንዲብራራላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!