
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡
የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2016 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ከሕዝብ የቀረቡ ጥያቄዎችን ለገንዘብ ሚኒስቴር አቅርቧል፡፡
በዚህም መሠረት፦
👉 በሚቀጥለው ዓመት የሥራ ቅጥር የለም ተብሏል፤ ነገር ግን ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ወጣቶች ብዙ ናቸው፤ ይሄን ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?
👉 ለዚህ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተና ካለፋችሁ ቀጥታ ሥራ ትመደባላችሁ ተብሎ ቃል ተገብቶ ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ ቅጥር እንደሌለ በመንግሥት ተገልጿል፤ ይህን እንዴት ታዩታላችሁ?
👉 የኑሮ ውድነት ቀን በቀን እየጨመረ እየመጣ ነው፤ ዜጎች በጦርነት እና በሕገወጥ ቤት ፈረሳ እየተፈናቀሉ ነው፤ ሥራ አጥ እየበዛ ነው፤ ለዚህ ሁሉ ችግር መንግሥት በሚቀጥለው ዓመት ምን አይነት መፍትሔ አስቀምጧል?
👉 የትምህርት ቤት ክፍያ ጨምሯል፤ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ለመጨመርስ መንግሥት ምን አስቧል?
👉 መንገዶች ተጀምረው በበጀት እጥረት ምክንያት ቆመዋል፤ በ2016 ዓ.ም በጀት ተጀምረው የቆሙ መንገዶችን ለመጨረስ ምን ታስቧል?
👉 አርሶ አደሮች የማዳበሪያ ችግር ገጥሞናል፤ መንግሥት አስፈላጊውን በጀት መድቦ ለምን በሰዓቱ እንዲቀርብ አያደርግም? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸውን አንስቷል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!