
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአማራ ክልል ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በክረምት በጎፈቃድ ይሳተፋሉ ተብሎ ታቅዷል። ወጣቶች የሰለጠኑበትን ዘርፍ መሰረት ያደረገ የሙያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው የተባለው ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፤ ምሩቃን ወጣቶችንና ባለሙያዎችን ተሳታፊ የሚያደርገው የሙያ የበጎፈቃድ አገልግሎት ተግባር በዕቅድ እየተመራ ነው ተብሏል።
በአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ የሥራ ሂደት ተተኪ ዳይሬክተር አለምነው ጌታሁን ለአሚኮ እንደተናገሩት በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልገሎት” በጎ ፈቃደኞች በሙያቸው የሚያገለግሉበት አሠራር ተዘርግቷል” ብለዋል።
ለክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የበጎነት አሻራቸውን የሚያሳርፉባቸው 13 የሥራ ዘርፎች ተለይተዋል፣ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅትም ተደርጓል ነው ያሉት አቶ አለምነው።
እስከ ባለፈው ሳምንት ባለው መረጃ መሰረትም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ አለምነው ሰኔ 27/2015 ዓ.ም በይፋ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ለአገልግሎት የተለዩ የሥራ ዘርፎችም በጎ ፈቃደኞች በሰለጠኑበት ሙያ እንዲያገለግሉ የሚያስችሉ ነባራዊ ሁኔታዎች፣ የሥራ መሳሪያዎችንና የሥራ ዘርፎችን የመለየት ተግባር ስለመከናወኑም አስገንዝበዋል። አገልግሎቱ ከሚሰጥባቸው ተቋማት ጋርም ቅንጅታዊ አሠራሮች ተዘርግተዋል ነው ያሉት።
በጎ ፈቃደኞች በሙያቸው ከሚያገለግሉባቸው ዘርፎች መካከልም ትምህርት፣ ግብርና፣ ጤና፣ ከተማ ጽዳትና ውበት እንዲሁም የዲዛይን ሥራዎችን የጠቀሱት አቶ አለምነው በበጎ ፈቃድ ለዜጎች ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጡ አስቻይ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
እንደ አጠቃላይ በክልሉ ከሚከናወኑ 13 የሥራ መስኮች ከ12 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎትም ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል ነው የተባለው።
ነገ በይፋ የሚጀመረው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እስከ መስከረም 15/2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ እንደኾነም ተገልጿል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!