የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ የፀጥታ ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ ተካሄደ።

49

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ የፀጥታ ዕቅድ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙበት የምክክር መድረክ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ የወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የምክክር መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ትውልድ የሚቀረፅበትን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም እንደ አንድ ትልቅ ተልዕኮ ወስዶ በኃላፊነት መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በሀገራችን የተካሄደው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የትምህርት ጥራት ችግር የቀረፈና የትምህርት ፖሊሲን የፈተሸ መሆኑን አስታውሰው ከሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በ102 የፈተና ጣቢያዎች የሚካሄደው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታውንና የክረምቱን የአየር ሁኔታ ያገናዘበ በርካታ የሰው ኃይል መመደቡን ተናግረው ፈተናው ከኩረጃ በፀዳ መልኩ እንዲካሄድ ሁሉም ኃላፊነቱን ወስዶ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የጋራ የፀጥታ ዕቅዱን ባቀረቡበት ወቅት በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በፈተና ጣቢያዎች የፀጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም ተማሪዎች ለፈተና ሲመጡ የሀኪም ማዘዣ የሌለው መድሃኒት በሽሮፕም ሆነ በታብሌት፣ የህክምና መስጫ መርፌ፣ የአንገት ሀብል፣ የፀጉርና የጆሮ ጌጥ፤ ከጋብቻ ቀለበት ውጭ ፈርጥ ያለው የጣት ቀለበት እና የእጅ አንባር አድርጎ፤ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ስልክ፤ አይ-ፓድ፤ ታብሌት፤ ላፕቶፕ፤ ስማርት ሰዓት፤ ሲዲ፤ ሚሞሪ፤ ሚሞሪ ሪደርና ኦ-ቲጂ ኮንቨርተር እንዲሁም ፎቶ የሚያነሱ እና ድምፅ የሚቀርፁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የተከለከሉ መሣሪያዎችን በዩኒቨርሲቲዎቹ ግቢ ውስጥም ሆነ በዙሪያው ይዞ መገኘት፣ ፈተና ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል መግባት እና ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ሳይሞላ ከፈተና ክፍል መውጣት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ግቢ ወስጥ በግልም ሆነ በቡድን ከፍተኛ ድምጽ ማሰማት የተከለከለ መሆኑንና ይህንን ተላልፎ በተገኘ ተማሪ ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ለመቀየር ከፍተኛ በጀት መድቦ ቀላል የማይባሉ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሀገራዊ የፀጥታ ተልዕኮው በተጨማሪ የትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እየሠራ ካሉት ሥራዎች ይህ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል ።

ከዚህ በፊት በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ከተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በተሻለ መልኩ እንዲካሄድ አንዳንድ የትራንስፖርት ችግሮችን መቅረፍ፤ ለተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጀምሮ በወረዳና በዞን ትምህርት ቢሮ አማካኝነት የፈተና ኦረንቴሽኖችን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። መረጃው የፌደራል ፖሊስ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አርባምንጭ ከተማ ገቡ።
Next article“በጎ ፈቃደኞች በሙያቸው የሚያገለግሉበት አሠራር ተዘርግቷል” የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ