
ፍኖተ ሰላም: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በ594 ትምህርት ቤቶች 40 ሺህ 14 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን እየወሰዱ እንደሚገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ኀላፊ ጌትነት ሙሉጌታ ፈተናው በዛሬው ዕለት በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በፈተና አሰጣጡ ዙሪያ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የገለጹት ኀላፊው በፈተና ወቅት ኩረጃ እንዳይኖር በአንድ ወንበር አንድ ተማሪን አስቀምጦ በመፈተን ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
ኀላፊው አክለው ፈተናው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የዞኑ የጸጥታ መዋቅር ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
አሚኮ የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን በፍኖተ ሰላም ከተማ እና በጃቢጠህናን ወረዳ የፈተና ጣቢያዎች ተዟዙሮ በተመለከተበት ወቅት ያነጋገራቸው የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ወንዳለ ሽባባው በከተማ አሥተዳደሩ በ6 የፈተና ጣቢያዎች 1ሺህ 114 ተማሪዎች ፈተና እየወሰዱ ነው ብለዋል።
የጃቢጠህናን ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው በወረዳው በ56 የፈተና ጣቢያዎች 3ሺህ 500 ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ መኾኑን ተናግረዋል።
ፈተናው በእስካሁኑ ሂደት ያለምንም ችግር እየተሰጠ መኾኑንም ኀላፊዎቹ ገልጸዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ተፈታኝ ተማሪዎች በበኩላቸው የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊ መኾኑን ገልጸው ፈተናውን ያለምንም ችግር ተረጋግተው እየወሰዱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ዛሬና ነገ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ መኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!