የምዕራብ ጠለምት ወረዳ ቦረቂ ችግኝ ማዘጋጃ ጣቢያን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር እየተሠራ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

67

ደባርቅ: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በርካታ የአማራ ክልል በርካታ ተቋማት ለጉዳት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡

በምዕራብ ጠለምት ወረዳ በውሕደት ቀበሌ የሚገኘው ቦረቂ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ ማዘጋጃ ፕሮጀክትም የሰላሙን መደፍረስ ተከትሎ ለችግር ከተጋለጡ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ይገኝበታል፡፡

ዛሬ ላይ ችግኝ ጣቢያው 10 ሺህ የሚጠጋ ችግኝ ተዘጋጅቶ ለአካባቢው አርሶ አደሮች እየተሰራጨ ይገኛል።

ወጣት ሙሃባው ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር የነበረው አቅም ትልቅ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ወጣቱ ፕሮጀክቱ ውጤት እንዲያስመዘግብ የድርሻውን ስለመወጣቱም ነው የሚናገረው። ወጣት ሙሃባው ገና በወጣትነቱ ነበር የፕሮጀክቱ ሠራተኛ ኾኖ የተቀጠረው። አሁን ላይ በመንግሥት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥያቄ አቅርቧል።

የምዕራብ ጠለምት ወረዳው የውሕደት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላቴ አስማረ ማሳቸው በማንጎ ችግኝ ተሞልቷል። ከተረጅነት ወጥተው ራሳቸውን የመቻል ሕልማቸውን እውን ለማድረግ አርፈው አያውቁም። ዛሬም ነገም ለልማት ተብሎ ከተሠጣቸው 2 ሄክታር መሬት ላይ ውለው ያመሻሉ። ቀን ቁፋሮ ማታ ውኃ ማጠጣት የዘወትር ተግባራቸው ከኾነ እነሆ አስር ዓመት አስቆጠሩ። ልፋታቸው ፍሬ አፍርቷል። የማንጎ ዛፋቸው ለምርት በቅቶ ጆንያቸው እስኪሞላ ለቅመዋል።

አርሶ አደሩ ከምግብነት አልፎ በዓመት ከ30 እስከ 40 ሺህ ብር መቁጠር ጀምረዋል። የቦረንቄ ፕሮጀክት በአካባቢያቸው መኖር ለኑሮአቸው መለወጥ ትልቁ ድርሻ ይወስዳል ብለዋል አርዶ አደር ሙላቴ። የችግኝ ጣቢያውን የበለጠ ወደ ሥራ ለማስገባት መንግሥት ተገቢውን ክትትል ቢያደርግ ሲሉም አንስተዋል።

የምዕራብ ጠለምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስለሺ በርሄ ፕሮጀክቱ ችግኝ አፍልቶ ለአርሶአደሮቹ ተደራሽ ማድረግ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እና የማንጎ ማዳቀያ ማምረትን ዓላማ አድርጎ መቋቋሙን ተናግረዋል። አቶ ስለሺ አካባቢው ሰፊ የውኃ አማራጭ ያለው እና ሰፊ ሊለማ የሚችል መሬት አለው ይላሉ። ፕሮጀክቱ ችግኝ በማዘጋጀት የአርሶ አደሮችን ቤት በበረከት ሞልቷል ነው ያሉት። በአርሶአደሮች ዘንድ ማንጎን ባሕል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ወደ ቀደመ አቅሙ እንዲመለስ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ የፕሮጀክቱን የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከር እየተሠራ ነው ብለዋል። ለ9 ወረዳዎች የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን ያቀርብ ነበር ያሉት ኀላፊው በሰላሙ መደፍረስ ችግር ላይ ቢወድቅም ዘላቂ የኾነ መፍትሔ ለማምጣት እየሠራን ነው ብለዋል። የችግኝ ጣቢያ ሠራተኞቹን በተመለከተ በፕሮጀክቱ ችግኝ እንዲዘጋጅ እና ከገቢው እራሳቸውን እንዲደጉሙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው አቶ ጌታቸው የነገሩን።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፕሬሽንን ከጅማሮ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ የሚያሳይ የፎቶ አዉደ ርዕይ ተከፈተ፡፡
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መሠጠት ተጀምሯል፡፡