
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል፡፡
በውይይቱ ክልሉ ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙት የጸጥታ እና ሰላም ችግሮች መነሻ ምክንያቶች፣ የተፈቱባቸው መንገዶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ይመክራል ተብሏል፡፡ ላለፉት ዓመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ክልሉ በርካታ ሰብዓዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ዋጋዎችን ከፍሏል ያሉት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ናቸው፡፡
“ሕዝቡ ከቆየበት ያልተረጋጋ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ነባራዊ ሁኔታ ወጥቶ ማኅበረሰባዊ እረፍት ይፈልግ ነበር ያሉት ዶክተር ጋሻው ነገር ግን ከውስጥም ከውጭም በሚወረወሩ አጀንዳዎች ሕዝቡ የሚፈልገውን ማኅበረሰባዊ እረፍት እንድናመጣ አላደረጉንም” ብለዋል፡፡
አንዳንዶቹ የጸጥታ ችግሮች የክልሉን ህልውና የሚፈታተኑ ነበሩ ያሉት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊው የሕዝቡ የሰከነ አካሄድ እና አስተዋይነት የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ ኀይሎች የፈለጉትን ያክል እንዳይሳካላቸው አድርጓል ብለዋል፡፡
ክልሉን ያጋጠሙት የሰላም እና ጸጥታ ችግሮች የውስጥ አንድነትን የሚፈታተኑ እና የክልሉን ሉዓላዊነት ለአደጋ አጋልጠው የሚሰጡ በመኾናቸው ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ከሰላም አማራጮች ባፈነገጠ መንገድ የሕዝቡን የሰላም እና የመልማት እድሎች እያጠበቡ ያሉ ችግሮች ላይ ሕግ ለማስከበር መሠራቱንም ዶክተር ጋሻው አንስተዋል፡፡ የጸጥታ ኀይሎች ቅንጅት፣ መናበብ እና ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት ያደረገ የእርምት እርምጃ ባይወሰድ ኖሮ አካባቢውን የግጭት ቀጣና ለማድረግ ሙከራዎች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ ችግሮቹ አሁንም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች አሉ፤ ሰፊ ውይይት ማድረግ፣ መመካከር እና ወደ ሰላማዊ የሃሳብ መንገድ ማምጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ካልተቻለ ግን የክልሉ ሰላም ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ሳይገባቸውም ኾነ ገብቷቸው የክልሉን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል የሚሠሩ ኅይሎች ከውስጥም ከውጭም አሉ ያሉት ዶክተር ጋሻው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡
እጅግ ተለዋዋጭ እና ማባሪያ የሌለው ውጫዊ ተፅዕኖዎች መኖራቸው በራሱ ችግሩን በዘላቂ መንገድ ለመፍታት ቅንጅት እና ትብብር ይጠይቃል ተብሏል፡፡ ሰላም የመልማት አጀንዳዎቻችን ማስፈጸሚያ ነው፣ ሰላም የሥነ-ልቦና ልዕልናን ለመጎናጸፍ የሚያስችል የፖለቲካ የበላይነትን መገንቢያ ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው “ሰላሙን ያጣ ሕዝብ በሂደት እና ቀስ በቀስ ሁሉንም ነገሩን ያጣል፤ ሰላም የሁሉም ነገራችን መሠረት ነው” ብለዋል፡፡ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጸጥታ ኀይሉ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!