
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ያለው መድረክ በክልል ደረጃ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ታሳቢ በማድረግ የአምስት ወር እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባውን ሥራ መገምገም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ግምገማው በዚህ ተግባር ላይ የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸውን ሥራዎች ለማስፋትና ድክመቶችን ለማረም እንደሚያግዝ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም መሐመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ውይይቱ በዋናነት የንግዱን ዘርፍ ተዋንያን በማወያየትና ግንዛቤያቸውን በማስፋት የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ፤ እንዲሁም የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ትስስር በማጠናከር የመንግሥት ሠራተኛውን እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች በአቅርቦቱ ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የእሑድ ገበያን በማስፋፋት የአምራቹንና የሸማቾችን አማራጭ ለማስፋት እንደሚያግዝም ተገልጿል።
በመድረኩ ግብይትን የሚያዛቡ ሕገወጥ ንግድና ሕገወጥ የደላላ እንቅስቃሴን ለማዳከም የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎም ይጠበቃል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርና የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ መምሪያ ኀላፊዎች የመንግሥት ሠራተኛውንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ የገበያ ማረጋጋት ሥራ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተሠራው ሥራም አበረታች ውጤት መታየቱን ነው ኀላፊዎቹ ያስረዱት፡፡ ተግባሩም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሥራ ኀላፊዎችና የምሥራቅ አማራ ንግድ መምሪያ የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!