በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን 5 ሺህ 368 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ መኾኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አሰታወቀ።

62

ሁመራ: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ105 ትምህርት ቤቶች 5 ሺህ 368 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን ዛሬ እየወሰዱ እንደሚገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረ ማርያም መንግሥቴ ገልጸዋል።

በፈተና አሰጣጥ ዙሪያ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የገለጹት ኀላፊው በፈተና ወቅት ኩረጃ እንዳይኖር በአንድ ወንበር አንድ ተማሪን አስቀምጦ በመፈተን ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።

ኀላፊው አክለው የተማሪዎች የፈተና አሰጣጥ ሂደት የተሳካ እንዲኾን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመኾን እያደረገ ላለው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ከትምህርት መምሪያ አካላት ጋር ሲከታተሉ ያገኘናቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ገብረ ዩሐንስ የሺነህ ተማሪዎች በሥነ ልቦና ብቁ ኾነው ለፈተና እንዲቀርቡ ሲያግዙ እንደነበር አንስተዋል።

ተማሪዎች ፈተናቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን የጸጥታ አካላትን በመመደብና ቁጥጥር በማድረግ መምሪያው የተግባቦት ሥራ እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እየተሰጠ ይገኛል።

ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ክልሉ የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጌዴኦ ዞን ወናጎ ከተማ ገቡ።