“ክልሉ የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

86

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወቅታዊ የሠላም እና ደህንነት ላይ መሠረት ያደረገ የግምገማ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ውይይቱ በክልሉ የተፈጠሩ የሠላም እና የጸጥታ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችን እና ሕግ የማስከበር ስምሪቶችን ይዳስሳል ተብሏል።

የሠላም እና ደህንነት ጉዳይ የአማራ ሕዝብ ወቅታዊ ቁልፍ አጀንዳ ነው ያሉት የአማራ ክልል ሠላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው። የክልሉን ሠላም እና ማሕበረሰባዊ ረፍት አደጋ ላይ የሚጥሉ በርካታ የጸጥታ ችግሮች ተፈጥረው ነበር ያሉት አቶ ደሳለኝ ችግሮችን በቅድሚያ በሠላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

ክልሉ በሀገሪቱ የተከሰቱ የሕልውና ስጋቶችን እስከ መስዋዕትነት የደረሰ ዋጋ በመክፈል የቀለበሰ ታላቅ ሕዝብ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ ለክልሉ አሁንም ድረስ አጀንዳዎችን በመወርወር አካባቢውን ሠላም የራቀው ቀጣና ለማድረግ የሚሰሩ አሉ ነው ያሉት።

የተለያየ ፍላጎት ያላቸው እና በውስጥም በውጭም ያሉ ኃይሎች የክልሉን ሠላም ለማወክ ቀን ከሌሊት እየሰሩ ነው። ችግሩ በተፈጠረበት መጠን ልክ ከቁጥጥር ውጭ ያልወጣው ከችግሮቹ በላይ የመሆን ሥነ-ልቦናዊ እና ታሪካዊ ልምድ ያለው ሕዝብ በመሆኑ ነው ብለዋል።

“ክልሉ የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት ነው” ያሉት አቶ ደሳለኝ ችግሮችን ገምግሞ እና አርሞ መውጫ በሮችን ማዘጋጀት ተገቢ መኾኑን አንስተዋል። የእርስ በእርስ ልዩነቶች አሸናፊም ተሸናፊም የላቸውም፤ ለችግሮቻችን የበሰለ መፍትሄ መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉን ሠላም እና ጸጥታ ማስከበር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ ደሳለኝ የጸጥታ ኃይሉ እና የፖለቲካ አመራሩ በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ያለፈ ታሪካችን እንደሚነግረን በጋራ ስንቆም ለላቀ ውጤት የበቃንባቸውን ጊዜያት አይተናል፤ ስንነጣጠል ደግሞ አቅሞቻችንን ጨርሰን ለውጭ ተጽዕኖ ተጋላጭ ሆነናል ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና መላው ሕዝብ ለክልሉ ሠላም መከበር እና ለሕግ የበላይነት መስፈን በጋራ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የስምንተኛ ክፍል ፈተና እየተሰጠ ነው፡፡
Next articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን 5 ሺህ 368 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ መኾኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አሰታወቀ።