
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የስምንተኛ ክፍል ፈተና እየተሰጠ መኾኑን ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ የስምንተኛ ክፍል የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ በክልሉ እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ 347 ሺህ 966 ተማሪዎች ተመዝግበው ፈተናውን ለመውሰድ ሲጠባበቁ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ፈተናው በ5 ሺህ 752 ትምህርት ቤቶች ነው እየተሰጠ የሚገኘው፡፡ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ፈተናው በታቀደለት መልኩ መጀመሩንም ገልጸዋል፤ ፈተናው ዛሬ እና ነገ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡
ትምህርት ቢሮው ከፈተናው አስቀድሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሠራ እንደቆየ ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኋላፊዋ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ ዓመቱን ሙሉ ሲሠራበት መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
ለፈተናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡ የቁሳቁስ ስርጭት በሁሉም የፈተና ጣብያዎች በተያዘለት ጊዜ እንዲደርስ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ፈተናውን የሚያስተባብር የሰው ኀይል ስምሪትም አስቀድሞ መሠጠቱን ነው የተናገሩት፡፡ ፈተናውን የሚያስፈትኑ እና የሚያስፈጽሙ አካላት የተሟላ ግንዛቤ መውሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎችም የተሟላ ግንዛቤ ወስደው ወደ ፈተና መግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ፈተናውን በአግባቡ ለመስጠት ከክልል ጀምሮ በቂ ዝግጅት ተደርጎ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ የፈተና ጉዳይ የተማሪዎች ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ፈተና የክልሉና የሀገር የክብር ጉዳይ ነው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት የሚሠሩት ነው ብለዋል፡፡
የፈተናው ውጤት የተማሪዎች፣ የመምህራን እና የወላጆች ውጤት መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ የተማሪዎች ውጤት የክልልና የሀገር ውጤት ነው ያሉት ኀላፊዋ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!