
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ መልካሙ ጌትነት እንደገለጹት ጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችን በዘጠኝ መስፈርቶች አወዳድሯል፡፡ በዚህም ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሁለተኛ ደረጃ ይዟል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ውድድሩም ማቻከል ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ መውጣቱን ተናግረዋል ኅላፊው።
ውድድሩ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን፣ የጤና ተቋማት መደጋገፍ፣ በየተቋማቱ ተመሳሳይ ሕክምና አገልግሎት መስጠት፣ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎ፣ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም፣ የሳኒቴሽን ግብይት ማዕከል ወይንም የተለያዩ ቁሶችን በማምረት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድርግና ደረጃውን የጠበቀ የጤና ኬላ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ባለፈው ዓመትም በዞኑ የሚገኘው የጁቤ ጤና ጣብያ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡
ዞኑ ከዚህ ባለፈ በክልሉ የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ከተሠራላቸው 45 ሺህ ሰዎች ውስጥ 13 ሺህ ሰዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ ቀዳሚ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም አጠቃላይ በክልሉ ከተሠራላቸው ሰዎች 28 በመቶ ይሸፍናል፡፡ ከዚህ ባለፈ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባላትን በማፍራት እና በገንዘብ መዋጮ ከእቅድ በላይ በመፈጸም በክልሉ ግንባር ቀደም መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
ዞኑ በ2014 ዓ.ም ከማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን 123 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ያነሱት ኀላፊው በዚህ ዓመት ደግሞ ወደ 228 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡ በኤች አይቪ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍም በክልሉ ግንባር ቀደም እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በጤና ጣቢያዎች የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታትም እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ገልጿል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!