
ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓይኔ የተቀደሰውን ሥፍራ አየች፣ እግሬ በተቀደሰው ሥፍራ ተመላለሰች፣ አፍንጫዬ እፁብ የሚያሰኘውን ማዕዛ አሸተተች፣ ጀሮዬ የከበረውን ታሪክ ሰማች፣ እጄ ቅዱሱን ሥፍራ ዳበሰች፣ ልቤ ሀሴትን አደረገች፣ አብዝታም ተደሰተች፡፡
ቅዱሳን የኖሩበት፣ የሚኖሩበት፣ ጻድቃን የሚመላለሱበት፣ ደጋጎች የሚጠለሉበት፣ በማዕልትና በሌሊት ያለማቋረጥ ምልጅና ጸሎት የሚደረስበት፣ ስብሐተ እግዚአብሔር የማይታጎልበት፣ ምስጢራት የሚነገሩበት፣ ጥበብ የሚመነጭበት፣ ታሪክ የመላበት ታላቅ ሥፍራ፡፡ ዓለምን የናቋት፣ አንይሽም ያሏት አበው ስጋቸውን አድክመው፣ መንፈሳቸውን አጠንክረው፣ በበዓት ተወስነው በዚያ ሥፍራ ይኖሩበታል፡፡
ውኃ በውኃ ላይ ባለፈበት፣ አድባራትና ገዳማት በመሉበት፣ ስውር ቤተ መቅደስ ባለበት፣ ደናግላን በሚኖሩበት፣ ቅዱሳን በሚከትሙበት፣ ባሕታውያን በሚመላለሱበት፣ ስውራን በዓታቸውን ዘግተው በሚጸልዩበት፣ ለምድር በረከትና ረድኤት በሚለምኑበት፣ የሰውና የመላእክት ኅብረት በማይለይበት፣ ቅዱስ መንፈስ በሚረብበት በምስጢራዊ ሐይቅ አንደበት ችሎ የማይናገራቸው፣ ጀሮ ችሎ የማይሰማቸው፣ ልብ ሆኖለት የማይመረምራቸው ከተዋቡበት የተዋቡ፣ ከተመረጡት የተመረጡ እጹብ የሚያሰኙ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሥፍራዎች መልተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ በሚነገርበት፣ ስርዓተ ክህነት እና ስርዓተ መንግሥት በጸናበት ሥፍራ ተገኝቻለሁ፡፡ ይህ ሥፍራ የቅዱሳን መኖሪያ፣ የበረከት ማደሪያ፣ የእውቀትና የጥበብ መፍለቂያ ነው፡፡ ትናንት ጥበብ ተቀድቶበታል፣ ዛሬም ይቀዳበታል፣ ነገም ይቀዳበታል፣ ጥበብን የሚሹ ሁሉ ይጠጡበታል፣ በጥበብም ይረኩበታል፡፡ ታላቁ ሥፍራ ርዕሰ አድባራት ወ ገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ፡፡ በዚህ ስፍራ ተመርምሮ ያልተደረሰባቸው፣ ታሪክ ነግሮ ያልጨረሳቸው፣ ሕዝብ ሁሉ የሚደነቅባቸው እና ይሰማቸው ዘንድ የሚጓጓላቸው ምስጢራት መልተዋል፡፡
እድል ቀንቶኝ፣ በተቀደሰው ሥፍራ ተገኝቼ፣ ከሊቁ እግር ሥር ተቀምጬ የከበረውን ታሪክ ሰምቻለሁ፡፡ በገዳሙ የአራቱ ጉባኤያት መምህር ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን እጅግ የበዛውን፣ እንደ ሐይቁ የሰፋውን ታሪክ ነግረውኛል፡፡ ዳሩ ያን ሁሉ ታሪክ እጽፈው ዘንድ ብዕሬ አቅም የላትም፣ ልቡናዬም ያን ሁሉ አትችልም፡፡ እንደ ሐይቅ ከሰፋው ታሪክ ጥቂቱን ጻፍኩ እንጂ፡፡
ታሪኩ ከብሉይ ዘመን ጀምሮ ይመዘዛል፡፡ ቀደምት ታሪክ ያላቸው ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ርዕሰ አድባራት ወ ገዳማት የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የብሉይ ኪዳን መሠረት ያለው፣ ቀደምት ታሪክ የመላበት ነውና ርዕሰ አድባራት ወገዳማት የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሲተረጉሙበት፣ ትምህርት ሲሰጥበት፣ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈጽምበት፣ የኦሪት መስዋዕት ሲሰዋበት፣ ስርዓተ ኦሪት ሲቀርብት የኖረ ታላቅ ገዳም ነው ጣና ቅዱስ ቂርቆስ፡፡
ይህ ስፍራ አስቀድሞ ደብረ ሳሂል ሳፍ ጽዮን ይባል ነበር፡፡ ደብረ ሳሂል ማለት የይቅርታ የጽዮን ተራራ ማለት ነው፡፡ ይህም የተባለው የደኅንነት መስዋኢት እየቀረበ ይቅርታ ይሰጥበት ስለነበር ነው፡፡ ዛሬም ድረስ መሰዋዊው አለ፡፡ ዘመናት አለፉ፡፡ ሌላ ዘመንም መጣ፡፡ በዚያ አካባቢ ቸነፈር በዛ፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ አንድ የበቁ ባሕታዊም ታቦተ ቂርቆስን ብታመጡ ቸነፈሩ ይርቃል፣ መቅሰፍቱም ይቆምላችኋል አሉ፡፡ የተባለውንም አደረጉ፡፡ የቅዱስ ቂርቆስ ታቦትም መጣ፡፡ ይህም ታቦት በቅዱስ አትናቲዮስ እጅ የተባረከ ነው፡፡ ረሃቡና ቸነፈሩ ጠፋ፡፡ ያንም ቃል ኪዳን በዚያች ምድር ጸንቶ ይኖራል፡፡ ስሙም ቂርቆስ እየተባለ ይጠራ ጀመር፡፡
ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ሲናገሩ ቤተ ክርስቲያን ትንቢት፣ ኦሪት፣ ታቦት፣ ሐዲስ፣ መስቀል፣ ታሪክ፣ ዘመነ አበው፣ ዘመነ ወንጌል፣ ዘመነ ሊቃውንት፣ ዘመነ መነኮሳት፣ ዘመነ ሰማዕታት ያላት እርሷ እንደ አሮን ልብስ ናት ይሏታል፡፡ ቤተክርስቲያን እውነተኛይቱ ሮማን ናት፡፡ ኢትዮጵያም የአሮንን ልብስ ትመስላለች፣ የሮማንም ወርቅም ያላት፡፡ ሁሉ ያላት ናት፣ ኢትዮጵያ ትክክለኛይቱ ሮማን ናት ይሏታል፡፡
ጣና ቅዱስ ቂርቆስም እንደ ሮማን ብዙ ጸጋ አለው፡፡ ጣዖታት የሚወድቁላት፣ ሕዝብ የሚሰግድላት፣ ትዕዛዝ የጸናባት፣ አምላክ የሰጣት ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ያረፈችበት ነውና፡፡ በአሥራ ሁለት ሺህ ሌዋዊያን በሊቀ ካህናቱ አዛሪያስ መሪነት የመጣችው ታቦተ ጽዮን የተቀመጠችበት፡፡ እግዜአብሔር በእጆቹ ትዕዛዘቱን የጻፈባት፣ በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጣት፣ ሙሴ አርባ ቀን ጾሞ የተቀበላት፣ በወርቅ የተለበጠችው፣ ለምድርም የተሰጠችው፣ ኪሩቤል የሚጋርዷት፣ የስርዬት መክደኛ ያላት ጽላተ ሙሴ በዚያ ሥፍራ አርፋች፡፡
አሮን የቀደሰባት፣ አሮን ያጠነባት፣ ሳሜኤል ያመሰገነባት፣ ዳዊት የዘመረባት፣ ነብያት ታምራትን ያደረጉባት፣ ሕዝብ ሁሉ የሰገደላት፣ የሚሰግድላት፣ ጣዖታት በፍርሃት የሚወድቁላትና ከምድረ ገጽ የሚጠፉላት፣ ጎሊያድን የቀጠቀጠችው፣ ዮርዳኖስን የከፈለችው፣ በሕብስትና በጎሞር የታጀበችው እውነተኛይቱ ታቦት ታቦተ ጽዮን በዚያ ሥፍራ አርፋለች፡፡
ሊቀ ካህናቱ የሚቀድሱባት፣ ምስጋናና ውዳሴ የሚያቀርቡባት፣ እግዚአብሔር ተገልጦ ለእስራኤል በረከት የሚሰጥባት፣ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ተቀምጣ የነበረችው፣ ለሰሎሞን ኃይልና ብርታት የሆነችው፣ ጥበብና ሞገስን የቸረችው፣ የመወደድና የመከበር ግርማ የሰጠችው፣ ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ታቦተ ጽዮን በርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቂርቆስ ገዳም አርፋለች፡፡
ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያለቀሱላት፣ የግብጽ ጣዖታት የወዳደቁላት፣ ሕዝብ ሁሉ የሚሰግድላት፣ ሰሎሞን ከእርሱ በራቀች ጊዜ ያለቀሰላት፣ የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያነቡላት፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ከእርሱ ጋር መሆኗን ባወቀ ጊዜ አብዝቶ የተደሰተባት ታቦተ ጽዮን በዚህ ቅዱስ ሥፍራ አርፋለች፡፡
ጣና ቂርቆስ፣ መርጦለ ማርያም፣ ተድባበ ማርያም እና አክሱም ጽዮን ማርያም አያሌ ታሪክ የሚቀዳባቸው፣ የጸና ሃይማኖት ያለባቸው፣ የኢትዮጵያ አንድነት የሚመነጭባቸው ናቸውም ይሏቸዋል አባ፡፡ እነዚህ ጥንታዊን አብያተክርስቲያናት የከበረ ታሪክ የመላባቸው ርዕሰ አድባራት ወገዳማት የሚል ስያሜ ያላቸው ጥንታውያን ናቸው፡፡ በቀደመው ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሲነግሥ የአራቱ ገዳማት ወ አድባራት መሪዎች ተገኝተው ካልጸለዩ በስተቀር አይነግስም ነበር፡፡ እነኚህ ታላላቅ ርዕሰ አድባራትና ወ ወገዳማት በትረ መንግሥት አስጨብጠው፣ በልብሰ መንግሥት አስጊጠው፣ ለንግሥና የተገባውን ቅባት ቀብተው እና እጅግ ያማረውንና የተወደደውን ዘውድ ደፍተው ያነግሡታል፡፡ መነኮሳቱና ካህናቱ ለንጉሡ ይጸልዩለታል፣ ደሃ እንዳይበድል፣ ፍርድ እንዳያጓድል፣ ትዕዛዛትን እንዳይሽር፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳይዝል ይጸልዩለታል፡፡ በጸሎታቸው ያበረቱታል፣ በምክራቸው እና በተግሳጻቸው በመልካሙ ጎዳና ያስጉዙታል፡፡
ንጉሡም በአምላክ ፈቃድ የተቀባውን የንግሥና ፈቃድ እያሰበ በምድር መልካሙን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ይታትራል፣ በቤተ መቅደስ እየተገኘ አምላኩን ያመሰግናል፣ ለጌታውም የተገባውን ያደርጋል፡፡ የአበውን ቃልና ተግሳጽም ያከብራል፡፡ ጣና ቂርቆስ የኢትዮጵያ ጥንታዊነት የሚገለጥበት፣ ስርዓተ መንግሥትም፣ ስርዓተ ክህነትም የሚጸናበት፣ የሐዲስ ኪዳን መሠረት የሚነሳበት ከከበሩት የከበረ፣ ከተመረጡት የተመረጠ ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡
ዘመነ ብሉይ ፍጻሜው ቀረበ፡ ነብያት የተነበዩለት፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ እንደሚወለድ አስቀድመው የተናገሩለት፣ አድማና ልጆቹ በተስፋ የሚጠብቁት፣ ሰማይና ምድር የማይወስኑት፣ ዘመናት የማይቆጠሩለት፣ አፍላጋትና ቀላያት በእፍኙ የማይሞሉት የጌታ መወለጃ ጊዜ ቀረበ፡፡ ጊዜው በደረሰ ጊዜም በድንግልና ከጸናች፣ ከፍጥረታት ሁሉ ከላቀችና ከተወደደች፣ በሀሳቧም፣ በስገዋም፣ በነብሷም ንጽሒት እና ብጽሒት ከሆነች እመቤት ተወለደ፡፡
በተወለደም ጊዜ ሄሮድስ የተባለ ንጉሥ ሕጸናትን ይገድል ነበርና ማርያም ልጇን ይዛ ተሰደደች፡፡ ወደ ኢትዮጵያም መጣች፡፡ በምድረ ኢትዮጵያም በብዙ ሥፍራዎች ተቀመጠች፡፡ እርሷ የተቀመጠችባቸውና ያረፈችባቸው ሥፍራዎችም የተባረኩ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በኢትዮጵያ ብዙ ሥፍራዎች ተቀምጣለች ኡደቷን የጨረሰችው ግን በጣና ቂርቆስ ነው ይላሉ አባ፡፡ ጣና ቂርቆስ የመጀመሪያው የሐዲስ ኪዳን ቅዱስ ቤተሰብ ማረፊያ ነውም ይላሉ፡፡ የአንድነት ምልክት ነው፡፡
በዚያች ቅድስት ምድር የተቀደሰችው እመቤት ለሦስት ወር ከአሥር ቀናት ተቀምጣበታለች፡፡ ያቺ ምድር የተቀደሰች ናት፡፡ ያቺ ምድር በበረከት የተመላች ናት፡፡ ያቺ ምድር በቅዱሳን የተከበበች፣ ያቺ ምድር በታሪክ የከበረች፣ ያቺ ምድር ሃይማኖትን ጠብቃ የኖረች ናት፡፡
ዘመኑ ደረሰ፡፡ ሄሮድስ ሞቷልና ተመለሱ የሚል ቃል መጣ፡፡ ጌታም እናቱን እንሂድ ባላት ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም ኢየሩሳሌም ሀገሬ ናት ነገር ግን ከእነ ልጄ አሰድዳኛለች፣ የዚህች ሀገር ሰዎች ደግሞ አያውቁኝም ያለ ሀገር ሀገር ሰጥተው ያኖሩኛል፣ ስለዚህ የምኖረው በዚህች ሀገር ነው፣ የዚህች ሀገር ሰዎች እግዚአብሔርን ይፈራሉ አለችው፡፡ ስለ ጽድቅ የሚደንግጥ ብጹዕ ነው፡፡ እንደተባለ ኢትዮጵያዊያን ልባቸው ሩህሩህ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘር አይመርጡም፣ ሀገር አይመርጡም ማንም ሰው ሲመጣ ይቀባለሉ፡፡
ልጇም ይሄን በሰማ ጊዜ እዛ ሄጄ የዓለምን ድኅነት እፈጽማለሁ፡፡ ይህችን ሀገር ከወደድሻት የአንቺ እርስት አድርጌ እሰጥሻለሁ አላት፡፡ አንቺም እነርሱን ትወጂያለሽ፣ እነርሱም በአንቺ ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ አላት፡፡ ጌታ እናቱ ማርያምን አንቺም የኢትዮጵያ እናት ሁኚ፣ ኢትዮጵያም የአንቺ ልጅ ትሁን አላት፡፡ ያን ቅዱስ ሥፍራ በየቀኑ እየመጣሽ ትጎበኝዋለሽ በማለት ቃል ገባላት፡፡ የከበረው ቃል ኪዳንም በዚያ ሥፍራ ተፈጸመ፡፡ ይህም ቃል ኪዳን እስከ ዘመነ ምጽዕት ድረስ ጸንቶ ይኖራል ይላሉ፡፡ አምላክ የወደደውን ስም ኢትዮጵያዊያን ሁልጊዜም ይጠሩታል፤ ይወዱታል፡፡ ማርያም ማርያም ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ሳያውቁ ተቀበሏት፣ ሲያውቋት የመበረከት ምንጭ ሆነቻቸው ነው ያሉኝ አባ፡፡ ኢትዮጵያ ለምን ለብቻ ተመረጠች? ለምንስ ለማርያም የአስራት ሀገር ተደርጋ ተሰጠች አድሎ አይሆንም ወይ? ለሚሉ ይላሉ አባ እንደ ሥራዋ የተሰጣት በረከት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በሥራ ቀድመናል፣ ኢየሩሳሌም የገፋችውን ኢትዮጵያ አመለከችው፣ ኢየሩሳሌም አሳደደችው፣ ኢትዮጵያ አስተናገደችው፣ይህች ሀገር ሽልማት ይገባታልና ታላቋን ሽልማት ማርያምን ሸለማት ይላሉ አባ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እነኋት እናትህ ብሎ ለዮሐንስ ከመስጠቱ አስቀድሞ ለኢትዮጵያ በሁለት ዓመቱ ሰጥቷል ነው ያሉኝ፡፡
ጊዜው ደረሰ፡፡ ጌታ የዓለምን መዳን ይፈጽም ዘንድ ወደ እስራኤል ሊመለስ ነው፡፡ ጸሐነ በደመና፣ በደመና ጫናት እንደተባለ፤ ማርያምም በደመና ተጭና ወደ እስራኤል ሄደች፡፡ ይህም ሥፍራ ጣና ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክ የተፈጸመበትም ጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ነው፡፡ ምህረት ለሚያደርጉ ለኢትዮጵያውያን የምህረት እናት ተሰጣቸው፡፡ እርሷ እናታቸው፣ እነርሱም የአስራት ልጆቿ ሆኑ፡፡
በምድራዊ ዓለም የታሪክ አባት የሚባለው ሄሮዳተስ ኢትዮጵያውያን ሩህሩዎች፣ ከመንገድ ዳር ድንኳን ተክለው የሚያበሉ፣ ሰውነታቸውን የሚያድስ የጠራ ተፈጥሯዊ ውኃ ያላቸው፣ ጨዋታ አዋቂዎች፣ ስርዓት ጠባቂዎች፣ ገራግሮች ናቸው ብሏል ይላሉ አባ፡፡ እግዚአብሔርን የሚያከበሩ፣ በትዕዛዙም የሚኖሩ፣ ማርያምም ሕግ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ናቸው ያለቻቸው ናቸው ኢትዮጵያውያን፡፡ ዛሬስ በእግዚአብሔር ፊት የተወደዱት ኢትዮጵያውያን አሉን? ይሄም ይቅር በሄሮዳተስ አገላለጽ ልክ የሚሆን ኢትዮጵያዊ ዛሬ አለን? ብለው ይጠይቃሉ ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን፡፡
ይህን ቅዱስ ሥፍራ ክፉዎች አልረገጡትም፣ አይረግጡትምም፣ ለምን ካሉ የሚጠብቀው ሃያል፣ የሚጠብቀው እሳተ ነበልባል፣ የሚጠብቀው የማይሞከርና የማይቻል ነውና፡፡ ይህ ታላቅ ስፍራ ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ነው፡፡ ስርዓተ መንግሥት፣ እና ስርዓተ ክህነት የጸናበት ነውና፡፡
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መስቀላቸው፣ ካባቸው በዚያ ሥፍራ ይገኛል፡፡ ታሪክ አጥፊዎች አልደፈሩትም፣ አይደፍሩትም፤ ሕንጻው አርጅቶ ታድሶ ያውቃል እንጂ ሃይማኖት የሌለው አጥፍቶት አያውቅም ይላሉ አባ፡፡
ዜማን ከመላእክት ተምሮ፣ አክሱምን በዜማ ቀድሶ፣ አንቀጸ ብርሃንን አድርሶ ቅዱስ ያሬድ ወደጣና መጣ፡፡ በዚያም ሆኖ ድጓውን ጻፈ፡፡ እርሱ የጻፈው ድጓ ዛሬም አለ፡፡ መስቀሉና ካባውም አለ፡፡ እርሱ ቀለም የበጠበጠባቸው ድንጋዮች ዛሬም አሉ፡፡ መምህር ኤስድሮስ ሦስት መቶ መጻሕፍትን በቃላቸው ያጠኑበት ስፍራም ነው ርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቂርቆስ፡፡ ማርያም ቁጭ ብላ የጸለየችበት፣ ቆማም የጸለየችበት፣ እጅግ የተወደዱት የእግሮቿ ኮቴ ያለበት፣ የአህያዋ ሰኮና በዓለት ላይ የሚገኝበት፣ የኢትዮጵያ ካርታ ከዓለት ላይ ተቀርጾ የሚገኝበት፣ የኦሪት መሰዊያ ዛሬም ድረስ ያለበት ሥፍራ ነው ጣና ቅዱስ ቂርቆስ፡፡ በዚህ ሥፍራ ታቦተ ጽዮንን ያመጣት የካህኑ የአዛርያስ መቃብርም ይገኛል፡፡
የማይጠወልግ ጌጥ፣ የማይረግፍ ፈርጥ ነው፡፡ በዚያ ገዳም ውስጥ የእኛ እንጂ የእኔ የሚባል የለም፡፡ የግል ሀብትና ንብረት የለም፡፡ ክርስትና አንድነት ነው፣ ሃይማኖት አንድነት ነው፣ አንድነት ከሌለ ኃይል የለም፣ ሞት ማለት መለየት ነው፡፡ የጥፋት ልዩነትን የሚወድ ሰው ካለ ሞቷል ማለት ነው፣ መለያየትን ካመጣ መሞት፣ መጥፋት ነው፣ አንድነት ማለት መኖር ማለት ነው ይላሉ አባ፡፡ በዚያች ሥፍራ ሰው ሁሉ የራሱን ፈቃድ ለእግዚአብሔር ፈቃድ አስገዝቶ ይኖራል፡፡
ሂዱ ቅዱሱን ምድር እዩት፣ ቅዱሱን ሥፍራ ዳብሱት፣ እጅግ የከበረውን ታሪክ ስሙት፣ ከማዕዛዎች ሁሉ የላቀውን ማዕዛ አሽትቱበት፣ መልካሙን ነገር ተመልከቱት፡፡ በዚያ ሥፍራ አለቶች ሳይቀር ታሪክን ይነግራሉ፣ ሃይማኖትን ያስተምራሉ፣ ቀደምትነትን ይመሰክራሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!