“ወቅቱ ከመቸውም ጊዜ በላይ መትጋትንና መብቃትን፣ ወደ እግዚአብሔርም መጮህን የሚጠይቅ ነው”ብፁዑ አቡነ አብርሃም

89

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት በከፍተኛ የትርጓሜ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ደቀመዛሙርት አስመርቋል።

በዚሁ እለት ኰኲሐ ሃይማኖት የካህናት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤትም በአጫጭር ሥልጠናዎች ያሰለጠናቸውን ካህናትና መምህራን አስመርቋል።

በደቀ መዛሙርቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዑ አቡነ አብርሃም ሰልጥኖ መመረቅ ንቃትን፣ ትጋትንና ብቃትን የሚጠይቅ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

ሀገረ ስብከቱ ዘመኑን የሚመጥን፣ ለዘመኑ መልስ የሚሰጡ ንቁ ሊቃውንትን እያፈራ እንደሆነ ብፁዑ አቡነ አብርሃም ገልጸዋል።

አቡነ አብርሃም ጊዜው እግዚአብሔር “ንጹህ ልብን ከሰላም ጋር፣ ሰላምን ከንጹህ ልብ ጋር” እንዲሰጠን የምንለምንበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው ነው ያሉት።

ሀገር ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታና የጥንታዊቷን የሀገር ባለውለታ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የገጠማትን ፈተና ተገንዝበን ፈጣሪ ምህረት እንዲያወርድልን መለመን ይገባል ብለዋል።

ብፁዑ አቡነ አብርሃም ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክትም “ወቅቱ መምህር ኾኖ መገኘትን የሚፈትን መኾኑን መረዳት ይገባል፤ ለማዳን ብቻም ሳይኾን ተጠልፎ ላለመውደቅም መጠንቀቅ አለብን ብለዋል።

“ወቅቱ ከመቸውም ጊዜ በላይ መንቃትን፣ መትጋትንና መብቃትን፣ ወደ እግዚአብሔርም መጮህን የሚጠይቅ ነው” ብለዋል ብፁዑ አቡነ አብርሃም።

የዛሬ ተመራቂዎች አልጫውን አለም የምታጣፍጡ፣ ለቤተክርስቲያኒቱም መድህን የምትኾኑ ያድርጋችሁ ያሉት ብፁዑ አቡነ አብርሐም “እውቀታችሁን ተጠቀሙበት” ሲሉም አሳስበዋል።

ማስተማርም መማር በራሱ ግብ አይደለም ያሉት ብፁዑ አቡነ አብርሃም ያስተማርናቸውን ቤተክርስቲያን ልትጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት።

ሙያቸው ወደ ሚመጥነው የሥራ ዘርፍ መመደብና የሚያገለግሉበትን እድል በማመቻቸት በኩል ሀገረ ስብከቱ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት ሊቃውንትን ለራሱ ብቻም ሳይኾን ለሌሎችም ሀገረ ስብከቶች መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፈጣሪ መለያየትን፣ ጥላቻን አርቆ፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድንትን እንዲያመጣም ተግቶ መጸለይ፣ መንቃት እና መብቃት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነብያት የተነበዩትን፣ ሐዋሪያት ያስተማሩትን ትምህርት ጠብቃ እያስተማረች ለዘመናት ዘልቃለች” መላእከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም
Next articleሰራዊቱ የኢኮኖሚ አቅሞ ለሌላቸው ነዋሪዎች ቤት የመሥራት እና የመጠገን ድጋፍ አደረገ።