
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በአራቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት በከፍተኛ የትርጓሜ ትምህርት ያሰለጥናቸውን ደቀመዛሙርትን አስመርቋል።
ሀገረስብከቱ በአራቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት ለ6 ዓመት የሰለጠኑ 33 ደቀ መዛሙርትን ነው ያስመረቀው።
ደቀመዛሙርቱ በሦስት የትምህርት አይነቶች በሐዲስ ኪዳን፣ በብሉይ ኪዳን እና በጽሐፍተ-ሊቃውንት የተመረቁ ናቸው ተብሏል።
በዛሬው መርኃ ግብር ለ6ወራት አጫጭር ስልጠናዎችን የወሰዱ ካህናትና መምህራንም ተመርቀዋል።
ኰኲሐ ሃይማኖት የካህናት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በ9 ዋና ዋና የሥልጠና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ካህናትና መምህራንን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላእከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም “ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነበያት የተነበዩትን፣ ሐዋሪያት ያስተማሩትን ትምህርት ጠብቃ እያስተማረች ለዘመናት ዘልቃለች” ብለዋል።
መንፈሳዊም ኾነ ስጋዊ ልማት የሚመጣው በስልጠና ነው ያሉት መላእከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ሀገረ ስብከታችን የሊቃውንት መፍለቂያነቱን አስጠብቆ እንዲዘልቅ የሚያስችሉ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው ብለዋል።
ባስተላለፉት መልእክት ቤተክርስቲያን አሉኝ ባለቻቸው መምህራን ተምራችሁ ተመርቃችኋልና በተማራችሁበትና በሰለጠናችሁበት ሙያ የአባቶቻችሁን ተግባር እንድትፈጽሙ፣ የቤተክርስቲያኗም የቁርጥ ቀን ልጆች እንድትኾኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።
ተመራቂዎችም የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት እንደሚተጉ ነው ለአሚኮ የተናገሩት።
በሐዲስ ኪዳን የትምህርት ዘርፍ ሥልጠናቸውን ተከታትለው ዛሬ የተመረቁት መርሐ ጽድቅ እሸቴ ዓለሙ በተማርኩት ትምህርት ከነበረኝ ኀላፊነት በበለጠ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ሌላው መምህር እንግዳው ሙጨ በበኩላቸው ቤተክርስቲያን ጥበብ፣ እውቀትና ታሪክን ከሳይንሱ ጋር በማዛመድ ለሀገር ልማት እድገትና የችግር ሁሉ መድህን ማድረግ አቅም አላትና በተማርነው ትምህርት የበኩላችን እንወጣለን ነው ያሉት።
ጉባኤ ቤቶቹ የአባቶቻችን ጥበብ፣ እወቀትና ባሕል ለዘመናዊ ዓለም ችግር መፍቻነት መጠቀም የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን ጭምር እየሰጡ ነው ያሉት ደግሞ የአራቱ ጉባኤያት ምስክር መምህርና የባሕር ዳር ሀገረስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ ናቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደ ሀገር ለገጠመን የሰላም እጦትም መፍትሔ ማምጣት አለባት ነው ያሉት።
ለዚህም የባሕር ዳር ሀገረስብከት በመንፍሳዊ ስልጠናዎቹ ከአዕምሮ ግንባታ እስከ ስእብና ግንባታ እየሠራ ነው ብለዋል።
ሃይማኖታዊ ጉዳዮች፣ ማኀበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚያለሙ የፕሮጀክት ሥራዎችም ጥናትን መሰረት አድርጎ ችግር ለመፍታት እየተሠራ እንደኾነም ነው የተናገሩት።
የዛሬ ተመራቂዎችም ሀገር፣ ሕዝብና ቤተክርስቲያን የሚጠቅሙ ፣ ኀላፊነታቸውንም የመወጣት አደራ የተጣለባቸው ናቸው ብለዋል።
በመርኃ ግብሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዑ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ አገልግሎት መምሪያ ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ እና ሌሎች ሊቃውንትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!