የግል ጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማሳደግ ወቅቱን መሠረት ያደረጉ አሠራሮችን በአዲስ የማውጣት እና ነባሮችን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጤና ቢሮ ገለጸ።

76

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የግል ጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች ማኅበር “የሕዝብና የግል የጤና ተቋማት አጋርነት ለጤናማ ማኅበረሰብ” በሚል መሪ መልዕክት 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዷል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት መኮንን አይችሉህም( ዶ.ር) እንዳሉት

ለግሉ የጤና ዘርፍ ፖሊሲ ተቀርጾ፣ ደንብና መመሪያ ወጥቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ከተደረገ 35 ዓመታትን ተቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት በተለይም ደግሞ የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት ዘርፉ በችግሮች ውስጥ ማለፉን ነው ያነሱት።

. የግል የጤና አገልግሎቱ ለመንግሥትም ኾነ ለግሉ የጤና ዘርፍ አዲስ መኾን

. መለኪያዎቹ ከአደጉ ሀገራት የተቀዱ መኾናቸው

. ተቋማቱ በተመሠረቱበት ወቅት መንግሥት ይከተለው የነበረው ርዕዮተ ዓለም የግል ተቋማትን የሚያበረታታ አለመኾኑ

. የግል ጤና ተቋማት እንቅስቃሴ ተናጠላዊ መኾን ለግሉ ጤና ሴክተር ዋና ፈተናዎች እንደነበሩ ነው ያነሱት።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በ2005 ዓ/ም መጨረሻ በክልል ደረጃ የግል ጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች ማኅበር ተመሥርቷል። ማኅበሩ ከተመሠረተ ጀምሮ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሠጠ ይገኛል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት አሁን ላይ በአማራ ክልል 3 ሺህ የሚኾኑ የግል የጤና ተቋማት ይገኛሉ። የክልሉን 35 በመቶ የጤና አገልግሎትም እየሠጡም ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጤናና ጤናነክ ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጌትነት ስንታየሁ በክልሉ የግል ጤና ሴክተሩ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የአገልግሎት አሰጣጡም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

በተለይም ደግሞ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ በጦርነቱ ወቅት የነበራቸው ሚናና በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸውን ነው ያነሱት።

የግል ጤና ተቋማት ወቅቱን መሠረት ያደረገ አገልግሎት እንዲሰጡ 29 መለኪያዎችን በአዲስ የማውጣት እና ነባሮችን የማሻሻል ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በቀጣይም ወቅቱን የሚመጥኑ መለኪያዎችን የማውጣትና ነባሮችንም የማሻሻል ሥራ ይሠራል ብለዋል።

በሥራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከማኅበሩ ጋር በመነጋገር እየፈቱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በተደጋጋሚ ከሙያ ሥነ ምግባር ውጭ በሚሠሩ ተቋማት ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኪነ-ጥበብ ለሀገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ ዘመን ተሻጋሪ ነው” ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ
Next article“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነብያት የተነበዩትን፣ ሐዋሪያት ያስተማሩትን ትምህርት ጠብቃ እያስተማረች ለዘመናት ዘልቃለች” መላእከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም