“ኪነ-ጥበብ ለሀገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ ዘመን ተሻጋሪ ነው” ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

82

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 15ኛው የአማራ ክልል ባሕል እና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ከሐምሌ 1/2015 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል፡፡

በፌስቲቫሉ በክልሉ የሚገኙ 21 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ባሕል እና እሴቶቻቸውን የሚገልጹ ዝግጅቶችን አድርገው ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ፌስቲቫሉ ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ተጋባዥ እንግዶች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዘመናት መካከል ሀገርን እንደ መገኛ፤ ሕዝብን ደግሞ እንደ መንገደኛ እያንሰላሰሉ ለትውለድ ካቆዩ ማኅበረሰባዊ እሴቶች መካከል ኪነ-ጥበብ አንዷ ነች፡፡ ሰዓሊው በብሩሽ፣ ገጣሚው በስንኝ፣ ሙዚቀኛው በዜማ እና ደራሲው በድርሰት ለሀገራዊ አንድነት ብዙ ሠርተዋል፡፡ ሀገር፣ ሕዝብ እና ተፈጥሮን አዋደው እና አላምደው ከትውልድ ትውልድ የሚወራረድ ባሕል እና ማንነት እንዲኖር የኪነ-ጥበብ ድርሻ የላቀ ነው ይባላል፡፡

ኪነ-ጥበብ በባሕል፣ በእምነት፣ በማንነት፣ በርእዮተ ዓለም እና በሃይማኖት የተለያየን ሕዝብ በማቀራረብ እና በማስተሳሰር በበርካታ የዓለም ሀገራት ባለውለታ እንደኾነ ይነገራል፡፡ ኪነ-ጥበብ ጥላቻን በፍቅር፣ መነቃቀፍን በመተራረም፣ መለያየትን በመገናኘት፣ ቂምና በቀልን በይቅርታ የማከም ምትሃታዊ ኀይል አላት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለኪነ-ጥበብ የተለየ ፍቅር እና ተሰጥኦ እንዳላቸውም ይነሳል፡፡ ምናልባትም እንደ ሀገር ዘመናትን አብሮ እና ጸንቶ ለመዝለቅ ኪነ-ጥበባዊ እሴቶቿ ድርሻ ሳይኖራቸው አይቀርም ይባላል፡፡

ዓላማውን በክልሉ የሚገኘውን ነባር እና ቱባ የኪነ-ጥበብ ባሕል ማስተዋወቅ ላይ ያደረገ የባሕል እና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ከሐምሌ 1/2015 እስከ ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

በፌስቲቫሉ ከ400 በላይ ጀማሪ እና አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አበበ እምቢያለ በተለይም ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የሚገኙ 21 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች በሚሳተፉበት 15ኛው የአማራ ክልል ባሕል እና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ላይ የክልሉን እምቅ የኪነ-ጥብብ እና ባሕል አቅሞች ወደ ቱሪዝም ገበያው ለማስገባት እና ለማስተዋወቅ አቅም ይፈጥራል ነው የተባለው፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የባሕል እና የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ሁሉም ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የራሳቸውን የባሕል እና የሙዚቃ ቡድን ይዘው ይቀርባሉ ያሉት አቶ አበበ ውድድሩን ለመዳኘት ታላላቅ ባለሙያዎችም እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በባሕል እና የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሉ ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከታላላቆቹ ባለሙያዎች ልምድ የሚያገኙበት እና ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደሚኾንም ገልጸዋል፡፡

“ኪነ-ጥበብ ለሀገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ ዘመን ተሻጋሪ ነው” ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው በባሕል እና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሉ ላይ ለዘርፉ ዘመን አይሽሬ አበርክቶ ያደረጉ የሕይዎት ዘመን ተሸላሚዎች ዕውቅና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡ የባሕል እና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሉን ለመታደም ከሁሉም ክልሎች ጥሪ የሚደረግላቸው ተጋባዥ እንግዶች ይታደማሉ ነው የተባለው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው በጀትና ድጎማ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ስር ኦዲት ሊደረግ ነው
Next articleየግል ጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማሳደግ ወቅቱን መሠረት ያደረጉ አሠራሮችን በአዲስ የማውጣት እና ነባሮችን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጤና ቢሮ ገለጸ።