
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ሁሉንም ክልሎች ከፌደራል መንግሥት የተሰጣቸውን በጀትና ድጎማ መሠረት በማድረግ በዋና ኦዲተር ስር ኦዲት ለማድረግ እንደሚሠራ ተገለጸ።
ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ሰኔ 20 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት እስካሁን የክልል ዋና ኦዲተሮች በየክልላቸው ምክር ቤት የተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት በማድረግ የኦዲት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል ።
ኦዲቱም የሚሠራው የፌደራል መንግሥት መመሪያና ደንብን መሠረት በማድረግ ሳይኾን የየክልሎቹን መሠረት በማድረግ በመኾኑ ተጠያቂነት ሲኖርም ጉዳዩ የሚታየው በክልሉ ነው ያሉት። ለቀጣይ ግን ለተጠያቂነት በሚመች መልኩ ገንዘብ ሚኒስቴር ብሩን ሲለቅ ክልሎች ከራሳቸው ገቢ ለይተው እንዲመዘግቡና ለይተው ሪፖርት እንዲያቀርቡም ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል ።
ክልሎች ከፌደራል መንግሥት የሚሰጣቸውን በጀት ሲጠቀሙ በየምክር ቤታቸው በማጽደቅ ከራሳቸው ገቢ ጋር ደርበው በመቀላቀል ነው። በመኾኑም ይህንን ለማስተካከል የፌደራል መንግሥት ለክልል የሚሰጠውን በጀት፤ ርዳታና ድጎማ ኦዲት በተመለከተ ድግግሞሹን ለማስቀረት በ2013 ዓ.ም አዲስ አዋጅ እንዲፀድቅ ተደርጓል ብለዋል።
በተደጋጋሚ ኦዲት ማድረግ በኦዲት ተደራጊዎች ላይ ጫና ስለሚፈጥር የክልል ኦዲተሮችን አቅም በማጎልበት እነሱ የሠሩትን ለመቀበል የሚያስችል መመሪያም ባለፈው ዓመት ጸድቋል። በዚህ መሠረት ከየክልሉ ባለሙያዎች በማሠልጠንና ከፌደራልም ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን በመመደብ እየተሠራ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ይህ አሠራር በተለያዩ ምክንያቶች ከአዋጁ ወጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ኦዲተሯ በአሁኑ ወቅት ግን ከፌደራል መንግሥት የሚለቀቅ ገንዘብ ኦዲት የሚደረገው በዋና ኦዲተር ስር በመኾኑ አዲስ በወጣው አዋጅ መሠረት ከክልሎች ጋር ስምምነት ተደርጓል ሲሉም አስረድተዋል፤ ሊያሠራ የሚችል የጋራ መመሪያ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
በዚህ ዓመትም አማራ ክልል በጦርነት ውስጥ ስለነበር በሙከራ ደረጃ በአራት ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ፤ አዲስ አበባ፤ ሲዳማና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ ተተግብሯል። ይህ አሠራር ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሁሉም ክልሎች በሕጉ መሠረት በዋና ኦዲተር ስር ኦዲት የሚደረጉ ይሆናል።
በተመሳሳይ ከክዋኔ ኦዲት ጋር በተያያዘም ዋና ኦዲተሯ እንደተናገሩት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንም ኾነ የልማት ድርጅቶችን በተመለከተ ዘንድሮ 33 ተቋማት ኦዲት ተደርገዋል ነው ያሉት። በቀጣይ አርባ ለማድረስ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
እንደ ኢፕድ ዘገባ ተቋሙ የመንግሥትና የሕዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲባል ሕዝባዊ ድርጅቶችን የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን እነዚህም እንደ ዐቃቤ ሕግ፤ ፓርላማና ፖሊስ ከመሳሰሉ ሦስተኛ ወገን የሚመጣ ጥያቄን መሠረት በማድረግ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!