
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለሁለተኛው አዲስ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ የብቃት መግለጫ መጠየቂያ ሰነድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ፈቃዱን ለመውሰድ ፍላጎት ያላቸው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢዎች የብቃት መግለጫ ሰነዳቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለተኛውን አዲስ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ (License B) የመስጠት ሂደቱን በማስቀጠል በሕዳር 2015 ማንኛውም ፍላጎት ያላቸው አካላት በፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ያላቸውን አስተያያት እንዲያቀርቡ በመጠየቅ ለአንድ ወር የቆየ ምክክር ማካሄዱን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ በዚህ የምክክር ሂደት ወቅት የተቀበላቸውን አስተያየቶች በመመርመር በፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ እና በፈቃዱ ላይ ግልጽና ምቹ የመወዳደሪያ መስክ ለመፍጠር ያስችላሉ ያላቸውን ማሻሻያዎች ማድረጉን ጠቅሷል።
በዚሁ መሰረት ባለሥልጣኑ በፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢዎች ከዛሬ ጀምሮ የብቃት መግለጫቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
በፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰጪዎች በ etlicenseB@eca.et ላይ የኢሜይል መልእክት በመላክ የብቃት መግለጫ ሰነዱን መጠየቅ እና ማግኘት እንደሚችሉ አመልክቷል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ አገልግሎት አቅራቢዎቹ የብቃት መግለጫ ምላሻቸውን እስከ መስከረም 4 /2016 እንዲያስገቡ የጊዜ ገደብ እንደሰጣቸው ጠቁሟል።
የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ መንግሥት በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ውስጥ እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲኖር ለማስቻል ካቀዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች አካል መኾኑን ባለሥልጣኑ ያስታወቀው።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግሉ ዘርፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኦፕሬተር ፈቃድ (License A) የተሰጠው ግንቦት 2013 በሳፋሪኮም ቴሌኮሙኒኬሽን ኢትዮጵያ ስም እየተንቀሳቀሰ ላለው ዓለም አቀፍ አጋርነት ለኢትዮጵያ የተባለ የግል ጥምረት መሆኑ ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!