ባሕር ዳር ከተማ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ መኾኑን አረጋገጠ።

73

ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ መድን ነጥብ መጣሉን ተክትሎ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ መኾኑን አረጋግጧል፡፡

ዛሬ በተከናወነው የ29ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ጨዋታ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 3 ለ 0 አሸንፏል፡፡

ደስታ ዮሐንስ በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲሁም ቢንያም አይተን እና አብዱል ከሪም ሞሐመድ (በራሱ መረብ ላይ) ግቦቹን አስቆጥሯል፡፡

ውጤቱን ተከትሎም በሊጉ ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባሕር ዳር ከተማ 2 ጨዋታዎች እየቀሩት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መኾኑን ያረጋገጠ ሲሆን የአፍሪካ ሻምፒንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ጨዋታዎች ውጤት ይጠብቃል፡፡

የአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን ባሕር ዳር ከተማ በውድድር ዓመት ምርጥ ውድድር ያሳለፈ ሲሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ተሳትፎን ማረጋገጥ ችሏል፡፡

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ጨዋታዎች እየቀሩት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መኾኑን ማረጋገጡ ይታወቃል፡፡

የሊጉ ሻምፒየን መኾን ከቻለ በአፍሪካ ሻምፒንስ ሊግ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአጼዎቹ ደረጃቸውን ወደ አራተኛ ከፍ ያደረጉበትን ድል አስመዘገቡ።
Next articleየኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለሁለተኛው አዲስ የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ የብቃት መግለጫ መጠየቂያ ሰነድ ይፋ አደረገ