“ከተሜነት መሰረተ ልማት በተሟላበት እና ጽዱ በኾነ ከተማ ውስጥ መኖር ነው” የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አገኘሁ ካሳ

55

ደብረ ታቦር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ ክምር ድንጋይ ከተማ ውስጥ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተመርቀዋል። ከተማዋ በጦርነት ከፍተኛ ውድመት ቢደርስባትም የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በመልሶ ግንባታ ላይ ትገኛለች። በከተማዋ በርካታ አዳዲስ የከተማ መሰረተ ልማት ግንባታዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ግንባታቸው የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን የዞንና የወረዳው አመራሮች ዛሬ መርቀዋል።ከተመረቁ መሰረተ ልማቶች ውስጥ ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፋ፣ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር የመንገድ ግንባታ፣ የመንገድ ላይ መብራቶች፣ የቁም እንስሳት የግብይት ቦታ፣ የውኃ ማፋሰሻ ቦይ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

የክምር ድንጋ መሪ ማዘጋጃ ቤት ከንቲባ ፍስሃ ባህሩ “የከተማ መሰረተ ልማት ሥራዎችን ሥንገነባ ትልቁ አቅማችን የከተማው ነዋሪዎች ናቸው” ብለዋል። በዚህ ዓመት ብቻ ከማኅበረሰቡ በጥሬ ገንዘብ እና በጉልበት በአጠቃላይ 6 ሚሊዮን ብር መዋጮ ተሰብስቧል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ 7 መቶ ሜትር የውኃ ማፋሰሻ ቦዮች፣ 2 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ፣ እና የመንገድ ዳር መብራቶች ተሰርተዋል ብለዋል። በአጠቃላይ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ስለመደረጉም ተናግረዋል።

ከተማዋን ከመሪ ማዘጋጃ ቤት ወደ ከተማ አሥተዳደርነት ለማሳደግ በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም አቶ ፍስሃ ተናግረዋል።

የጉና በጌምድር ወረዳ አሥተዳዳሪ አቶ ጌትነት አስናቀ ጉና በጌምድር ወረዳ ለአካባቢው ብሎም ለሀገር ልማት ቀናዒ የኾነ ሕዝብ ባለቤት ነው ብለዋል። የወረዳው ሕዝብ ከአመራሮቹ ጋር በመወያየት ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚኾን ገንዘብ እና ጉልበት ለማዋጣት ወደ ኃላ የማይል ስለመኾኑም ተናግረዋል።

አቶ ጌትነት በክልል እና በፌደራል መንግሥት ድጋፍ የሚሠሩ የመንገድ፣ የትምህርት ቤት እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። ማኀበረሰቡ የተሰሩ ልማቶችን በባለቤትነት መንከባከብ እና ማሥተዳደር እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አገኘሁ ካሳ ክምር ድንጋይ ከተማ ለሕዝብ ጥቅም የሚውሉ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ግንባር ቀደም ሥራ አከናውኗል ብለዋል። ከተማዋ በመሪ ማዘጋጃ ቤት ደረጃ የምትገኝ ቢኾንም ከእቅድ በላይ ገቢ በመሰብሰብም ከዞኑ ቀዳሚ ናት ብለዋል። በክምር ድንጋይ ከተማ በተለይም በጦርነት ከደረሰው ጉዳት ለማገገም እና አዳዲስ ልማቶችን ለመገንባት የተደረገው ጥረት እና ስኬት የሚደነቅ ነውም ብለዋል።

“ከተሜነት መሰረተ ልማት በተሟላበት እና ጽዱ በኾነ ከተማ ውስጥ መኖር ነው” ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው በክምር ድንጋይ ከተማ የተሠሩ መሰረተ ልማቶች የዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል። በክምር ድንጋይ ከተማ ውስጥ የተሠሩ አጠቃላይ ልማቶች በዞኑ ሁሉም ከተማዎች ተደራሽ እንዲኾኑ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

አቶ አገኘሁ ክምር ድንጋይ ከተማ ከታሪኳ እና ከሕዝቦቿ ልማት ወዳድነት አኳያ ተጨማሪ የልማት ሥራዎች ያስፈልጓታል ብለዋል። ለዚህም የዞኑ አሥተዳደር ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዚገም ቡና ልማት አምራቾች ኅብረት የዘርፍ ማኅበር ተመሠረተ።
Next article“የጥናትና ምርምር ተግባራት ለምናከናውነው ተቋማዊ ተግባርና አላማ አጋዥ ይሆናሉ።” አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ