
ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዚገም ወረዳ የዚገም ቡና ልማት አምራቾች ኅብረት የዘርፍ ማኅበር ተመስርቷል።
በአማራ ክልል የቡና ምርት አቅም እንዳለ ይነገራል። ነገር ግን ክልሉ ባለው አቅም ልክ ባለመሠራቱ በቡና ምርት በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳይኾን ቆይቷል። በአማራ ክልል ያለውን የቡና ምርት አቅም ለመጠቀም ባለሀብቶች በቡና ልማት እንዲሰማሩ ኹኔታዎች እንዲመቻቹ ሲደረግ ቆይቷል።
የዚገም ቡና ልማት አምራቾች ኅብረት የዘርፍ ማኅበርም ቡናን በሰፊው ለማልማት ዓላማ ይዞ ተመሥርቷል። ማኅበሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብ አልፎ ሀገርን ለመጥቀም ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ ነው ተብሏል። ቡናን እሴት በመጨመር አቀነባብሮ ለዓለም ገበያ የማቅረብ እና የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ሌሎች ምርቶች የመቀየር ዓላማ እንዳለውም ተመላክቷል። ለዚገም ወረዳ እና አካባቢው ማኅበራዊ አገልግሎት እንደሚሰጥና የወረዳውን ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ያለውን ተፈላጊነት ታሳቢ በማድረግ እንደሚሠራም አስታውቋል። ማኅበሩ ቡናን በአካባቢው በስፋት አለማለሁም ብሏል።
ከአሶሪት ትሬዲንግ የመጡት አክሊሉ መለሠ በዚገም ቡናን በስፋት ለማልማት በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ለቡና ልማት ትኩረት በመስጠት እያገዛቸው መኾኑንም አቶ አክሊሉ ነግረውናል፡፡
ማኅበሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ቡናን ለማልማት በሚያደርጉት ሥራ ባንኮች ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ቃል እንደገቡላቸውም ተናግረዋል። ማኅበሩን የመሠረቱት በልማቱ ዘርፍ ልምድ ያላቸው በመኾናቸው ውጤታማ እንደሚኾኑም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ እርሻ ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥፈፃሚ ቀረብህ መኮንን ባለሀብቱ በተሰጠው ጊዜና መሬት ላይ በትክክል ማልማት አለበት ብለዋል። ወደፊት ከመንግሥት መዋቅር ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ባለሀብቱ ሲደገፍ ራሱን፣ መንግሥትንና ሕዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት። ባለሀብቶች መንግሥት የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
የቡና ልማቱ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም ድጋፍ ማድረግ ይገባዋልም ብለዋል።
የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ኾነው የተመረጡት አሥራት አለባቸው የአማራ ክልልን የቡና ልማት ለማሳደግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በክልሉ የዚገም ወረዳ ቡናን በኩታ ገጠም ለማልማት መለየቱን ተናግረዋል። ቡና ለማልማት ለጠየቁ ባለሀብቶች ከ50 እስከ 400 ሄክታር መሬት ለመስጠት መፈቀዱንም ነው የተናገሩት። የተሰጣቸውን መሬት መረከብ እና ወደ ሥራ መግባት እንደቀራቸውም ተናግረዋል።
የቡና ልማት ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት አቶ አሥራት በአማራ ክልል የቡና ልማትን ለማሳደግ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ባለሀብቶች በተናጠል ኾነው ከሚሠሩት ባለፈ በማኅበር ሲሠሩ ሀብት ለማቀናጀት፣ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እና ሌሎች ጥቅሞች እንደሚኖሩትም አስገንዝበዋል። የቡና ልማትን በአማራ ክልል እናሻሽላለንም ነው ያሉት።
መንግሥት ለቡና ልማት የሠጠው ትኩረት ለሥራቸው እንደመልካም አጋጣሚ እንደኾነም አንስተዋል። ባለሀብቶች መሬት ጦም እንዳያድር እንደሚሠሩም ገልጸዋል። በአካባቢው የሚተገበረው የቡና ልማት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!