የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሥርዓተ ጾታ ዙሪያ የሚያካሂዷቸውን ምርምሮች የፖሊሲ ግብዓቶች ማድረግ ያስፈልጋል- ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

52

ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 3ኛውን ሀገር አቀፍ ሥርዓተ ጾታ እና ልማት ጉባዔ እያካሄደ ነው፡፡ “ሥርዓተ ጾታ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው ጉባዔ የተለያዩ ጥናቶች ለውይይት ቀርበዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ፋኩሊቲ የሥርዓተ ጾታ እና ልማት ትምህርት ክፍል ያዘጋጀው 3ኛው ሀገር አቀፍ ጉባዔ ለፖሊሲ አውጭዎች ግብዓት የሚኾኑ የጥናት ውጤቶች የሚገኙበት ነው ተብሏል፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋየ ሽፈራው (ዶ.ር) የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ነው ብለዋል፡፡

“ስለሥርዓተ ጾታ ስንነጋገር ቅድሚያ የሚመጣው የጾታ እኩልነት ጉዳይ ነው” ያሉት ዶክተር ተስፋየ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ግን ገና መሠራት ያለባቸው በርካታ የቤት ሥራዎች አሉብን ብለዋል፡፡ የሥርዓተ ጾታ የግንዛቤ ችግር በአንድ እና ሁለት ጥናቶች እና የመድረክ ላይ ንግግሮች የሚፈታ አይደለም፡፡ ለሥርዓተ ጾታ ትኩረት የሚሰጥ ማኅበረሰብ እና ተቋም እንዲፈጠር በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ጾታ ጉዳይን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነ ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበርካታ መንገዶች ስኬታማ እና ውጤታማ ለውጦች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሥርዓተ ጾታ አሠራር ሰነድ አዘጋጅቶ እየተገበረ ነው ያሉት ዶክተር ተስፋየ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችም ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡

ይህን መሰል ጉባዔ ዩኒቨርሲቲው በርእሰ ጉዳዩ እና በፈጻሚው የመንግሥት አካል መካከል ኾኖ የሚያቀርበው በመኾኑ ሀገራዊ ፍይዳው የላቀ ነው ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሥርዓተ ጻታ ዙሪያ የሚያካሂዷቸው ምርምሮች የፖሊሲ ግብዓቶች ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ተስፋየ በጉባዔው የሚሳተፉ አካላት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምሩ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ስለሥርዓተ ጾታ ጉዳይ ለመምከር እና ለመመራመር የሞራል እና የሥነ-ምግባር ጉዳይ ሳይቀር ያስገድዳል ያሉት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ጾታ እና ልማት ትምህርት ክፍል ኅላፊ መሠረት ዘውዱ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ ሥርዓተ ጾታ ላይ መነጋገር ሴቶችን ለማብቃት የሚያስችሉ የዕውቀት እና የግብዓት አቅሞች ይፈጠራሉ ብለዋል፡፡ ሥርዓተ ጾታ እና የጾታ እኩልነት ለማምጣት በርካታ የምርምር እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር መሠረት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አበረታች ሥረዎችን እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡

በጉባዔው ላይ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሳተፉ የውድድር ማስታወቂያ ወጥቶ በርካታ አመልካቾች ተሳትፈዋል ተብሏል፡፡ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተሳታፊ በኾኑበት በሦስተኛው ሀገር አቀፍ ጉባዔ ላይ 11 የምርምር ሥራዎች ይቀርባሉ፤ ከሚቀርቡት የምርምር ሥራዎች መካከል ስምንቱ ጥናቶች በሴቶች የሚቀርቡ ናቸው ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሟትም ስኬቶችንም አስመዝግባለች” ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
Next articleየዚገም ቡና ልማት አምራቾች ኅብረት የዘርፍ ማኅበር ተመሠረተ።