የቤዛዊት ተገጣጣሚ የሕንጻ አካል ማምረቻ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ፤ ፋብሪካው በርዕሰ መስተዳድሩና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል፡፡

691

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 26/2012ዓ.ም (አብመድ) የቤዛዊት ህንፃ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ (ሸኔል) በግንታው ዘርፍ የሚታየውን የጊዜና የውጪ ብክነት በመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተመስገን ጥሩነህ ተነገሩ፡፡

ቤዛዊት የሕንፃ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ በ2010 ዓ.ም ወደ ማምረት የገባ የግንታታ ግብዓት አምራች ነው፡፡ ፋብሪካው የነዳጅ ተረፈ ምርትንና እና ዚንክ ‹ኮትድ ጋልነቫንይዝድ ዋየር› በጥሬ ዕቃነት ይጠቀማል፡፡ የነዳጅ ተረፈ ምርት ከውጭ ሀገር የሚመጣ ሲሆን ዚንክ ኮትድ ጋልነቫንይዝድ ዋየር ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉ ብረታ ብረት ፋብሪካዎች ለማምረት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

ፋብሪካው ለቢሮ እና ለመኖሪያ ቤትነት የሚያገለግሉ የሕንፃ ተገጣጣሚ ወለል፣ ግድግዳ፣ ጣሪያ እና ደረጃ ይሠራል፤ ከጣሊያን ድርጅት ጋር ውል በመውሰድ እና ማሽነሪዎችን በመተከልም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ እስካሁን አምስት፤ አምስት የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ውል በመውድ በቤዛዊት ሕንጻ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ የግንባታ ሥራዎችን ማሠራታቸው ተነግሯል፡፡ ፋብሪካው ከ161 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት በባሕር ዳር ከተማ በ14 ሺህ ካሬ ሜትር ያረፈ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ደግሞ ዘርፉን ለማጠናከር 72 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

የግንባታውን የሥራ እንቅስቃሴ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተመሰገን ጥሩነህ እንደ ተናገሩት ቴክኖሎጂው ትምህርት ቤቶችን እና ጤና ጣቢያዎችን በፍትነት፣ በጥራት እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ለመሥራት የሚያገለግል ነው፤ መንግሥትም አዋጪ ስለሆነ በስፋት ይጠቀማል፡፡ በተለይም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሩቅ ቀበሌዎች ላይ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን በቀላሉ የግንባታ መሳሪዎችን አጓጉዞ ለመሥራት እንደሚጠቅም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ፋብሪካውም ተወዳዳሪ የለኝም›› ከሚለው ሐሳብ በመውጣት ጥራት ያለቸውን ሥራዎች በመሥራት ተወዳዳሪ እና የሕዝብ አገልጋይ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ አማካሪዎች እና ተቋራጮች የጀመሯቸውን ሥራዎች በፍጥነት አጠናቅቀው ለአግልግሎት ክፍት እንዲሆኑ በሙሉ ተነሳሽነት መሥራት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) ደግሞ በክልሉ የሚገኙ የዳስ ትምህርት ቤቶችንና አዳዲስ ትምህት ቤቶችን በቤዛዊት ሕንጻ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ ለማሠራት ዕቅድ እንደቀረበ ገልፀዋል፡፡ ፋብሪካውም በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ ይዞት የመጣው አዲስ ቴክኖሎጂ ፈጣንና ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ፋብሪካውም ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት የሚታየውን የውጭ ምናዛሬ እጥረት በመቅረፍ በስፊው ወደ ሥራ መግባት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እና የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ፋንታሁን ወንዴ ቤዛዊት ሕንጻ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ በወጪ በኩል 30 በመቶ እና በጊዜ በኩል ደግሞ 40 በመቶ ቅናሽ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በግንባታ ዘርፍ የሚታየውን የተበላሸ አሠራር የሚያስቀር እና ሁሉም ሥራ ተቆጥሮ የሚሠራበትን አሠራርን የፈጠረ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እስካሁን አምሥት የመንግሥት እና አምሥት የግል ድርጅቶችን ቢሮ እና ቤቶችን መሥራታቸውን ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ 550 ሰዎች ተመዝግበው የተወሰኑት ሥራ መጀመራውንና ቀሪዎቹ ግን ቴክኖሎጂው አዲስ በመሆኑና በበቂ ባለመረዳታቸው ደፍረው ወደ ሥራ አለመግባታቸውን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ፋብሪካው በሙሉ አቅም ወደ ሥራ የገባ በመሆኑ በግንባታ ዘርፍ ለመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ አግልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል›› ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous article‹‹የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን ወደ ኋላ ለማለት የሚሞክሩ ወደ ኋላ ይቀራሉ፤ ጥያቄው ግን ይቀጥላል፡፡›› አቶ ዮሐንስ ቧያለው
Next articleየፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ መሪዎች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና መሠረታዊ እሳቤዎች ላይ እየተወያዩ ነው፡፡