“ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሟትም ስኬቶችንም አስመዝግባለች” ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

61

ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም ከውስጥና ከውጪ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የፌዴራል እና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዓመታዊ የጋራ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ 5ኛ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

በሀገሪቱ የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ሁሉም ጠንካራ የሚዲያና እና ኮሙኒኬሽን ተግባቦት ሥራ ድጋፍ እንደነበራቸው ጠቅሰው ስኬቶቹ ግን በርካታ ፈተናዎችም እንደነበሩባቸው አንስተዋል፡፡

በተለይም ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደ ሀገር ሲፈትኑን ነበር ማለታቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይም በትክክለኛ መረጃ ላይ ከመመስረት ይልቅ በሐሰት በሚነዙ አሉባልታዎች አንዱን አካባቢ ከሌላው ጋር ለማጋጨት ሲፈጸሙ የነበሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች ትልቅ ፈተና እንደነበሩ ነው ያስረዱት፡፡

አሁን በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም ዘርፎች የተጀመሩት ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል፡፡

በቀጣይ 2ኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ ተግባራዊ የሚደረግበት በመሆኑ ሁሉም አካላት በመናበብ እንዲሠሩ አሳስበዋ፡፡

በሁሉም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተቀናጀ፣ የተናበበ እና ውጤታማ የተግባቦት ሥርአትን መዘርጋት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በተለይም በትምህርት ዘርፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚከናወኑ ሥራዎች እና በጤናው ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ሰፊ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሽፋን እንዲሠጣቸው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል በክልሎችና በተቋማት የኮሙኒኬሽን መዋቅር የተደረገው ምልከታ ውጤት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት መድኃኒት ለደሴ ከተማ፣ ለደቡብ እና ለሰሜን ወሎ ዞኖች ድጋፍ አደረገ።
Next articleየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሥርዓተ ጾታ ዙሪያ የሚያካሂዷቸውን ምርምሮች የፖሊሲ ግብዓቶች ማድረግ ያስፈልጋል- ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ