
‹‹የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን ወደ ኋላ ለማለት የሚሞክሩ ወደ ኋላ ይቀራሉ፤ ጥያቄው ግን ይቀጥላል፡፡›› አቶ ዮሐንስ ቧያለው
ክልሉ የሕዝቡን ኅልውና ለመጠበቅ እና ኢኮኖሚውን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ በኮሎምበስ ነዋሪ አማራዎች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ በሰሜን አሜሪካ-ኮሎምበስ ሕዝባዊ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ውይይቱ በወቅታዊ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በክልሉ ልማት እና ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው ነዋሪዎቹን ያወያዩት፡፡ ‹‹የአማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ ልዕልና›› በሚል መሪ መልዕክት በተካሔደው ምክክር በኮሎምበስ እና አካባቢው የሚኖሩ አማራዎች ተሳትፈዋል፡፡
በአማራ ጉዳይ ከተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት አዴፓ ስላለው ዝግጁነት፣ ስለወልቃይት ጠገዴ እና ሌሎችም የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች፣ በክልሉ የኢንቨስትመንት እና የሰላም ጉዳይ ከተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያዬቶች ቀርበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የአማራ ተማሪዎች ደኅንነት ላይ እየተፈጸመ ያለውን በደል ማስቆም ትኩረት እንዲሰጠው እና ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ አማራዎች ውክልና ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ አዴፓ ምን እየሰራ እንደሆነም ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ የትምህርት ቤቶችን የጥራት ችግር ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ከገንዘብ ጀምሮ በሚፈለገው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያረጋገጡት ተሳታፊዎቹ ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ምቹ እና ቀልጣፋ አሰራሮችን መተግባር እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ጠንካራ እና የተደራጀ ሕዝብ የመፍጠሩ ጉዳይ የራሳችን የሕዝቡ መሆኑን ተገንዝበን በተግባር ማረጋገጥ አለብን›› ብለዋል ተሳታፊዎቹ፡፡ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፣ የወሰን እና ማንነት ጥያቄዎች የሚመለሱበት፣ ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ አማራዎች በሀገራቸው በነጻነት የሚኖሩበት እና የሚወከሉበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲኖር ማስቻል ይገባል የሚለው የአዴፓም የሕዝቡም አጀንዳዎች ሆነው እየተሰራባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ በሰጡት ማብራሪም ‹‹የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን ወደ ኋላ ለማለት የሚሞክሩ ወደ ኋላ ይቀራሉ፤ ጥያቄው ግን ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡ ህጋዊ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራባቸው መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሰላምን በማስጠበቅ የክልሉን ልማት የማሳደግ ጉዳይ እየተሰራበት እንደሆነም ነው የሥራ ኃላፊዎቹ የተናገሩት፡፡
አቶ መላኩ ፈንታ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ የአማራ ሕዝብ በየትኛውም መልኩ በመደራጀት የፍትህ፣ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የመልማት ጥያቄዎቹን የማስመለስ አቅም መፍጠር እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም በዴንቨር፣ ሚኒሶታ፣ ሲያትል እና ሳንሆዜ ተመሳሳይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ መርሀ ግብሩ ያሳያል፡፡
ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ- ከኮሎምበስ- ኦሀዮ