የኢትዮጵያ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ከማኅበረሰባዊ ባሕልና ከሃይማኖቶች የተቀዳ ድንቅ እሴት መኾኑ ተገለጸ።

119

ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አለመግባባቶችን፣ግጭቶችን፣በደልንና ቂም በቀልን በሽምግልና የመፍታት ጉዳይ ለዘመናት የኖረ የኢትዮጵያ እሴት ነው። ምናልባትም ዓለም ዘመናዊ የግጭት አፈታትና የዳኝነት ሥርዓትን ሳይዘረጋ፣ ለፍትሕ መስፈን የተበደለን ክሶ የበደለን ደግሞ ወቅሶ በመዳኘት ዘመናዊው የሕግና ፍትሕ ሳይንስ ሳይቀመር ፣ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና በደሎችን እንዲታረሙ የሕዝብ ኹነኛ መዳኛ ነበር።

ዛሬም ቢኾን ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ፋይዳውን ተረድቶ በልኩ ለተጠቀመበት የዘመኑ የፍትሕ ሥርዓት ያልቀደመው የመፍትሔ መንገዶችን ይዟል ነው የሚባልለት። እንደ እድሜው መርዘም ፣ የፍትሕ አምባ ነውና ልንጠብቀው፣ልናጎለብተው፣ልንጠቀምበትና ለትውልድ ልናሻግረው ይገባል የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ነው።

ደራሲ፣ የባሕልና ታሪክ ተመራማሪው ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን በአማራ ክልል የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓት ማኀበር ሊቀመንበር ናቸው። ድንቅ የኢትዮጵያ እሴት ነው የሚባልለትን ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ሲያብራሩ ሽምግልና ከሁለት የሀገር መሰረቶች የተቀዳ ድንቅ እሴት ነው ይሉታል፣ ከማኅበረሰባዊ ባሕል እና ከሃይማኖቶች።

በቀደሙት ዘመናት ሽምግልና ከኅብረተሰቡ ወግ፣ልማድና ባሕል ተቀድቷልና ቅቡልነት ነበረው፣ከሃይማኖት ውግንና አለውና ክብርና መታመኑም የላቀ ነበር ይላሉ ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን።

የበዳይን ድርጊት አውግዞ ነገር ግን በዳይን ያላረቀ፣ የተበደለን ክሶ ከበዳይ ያላቃቃረ ፍርድ ከባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ፍትሕ አለችና ተከታይዋ እልፍ ነበር ነው የሚሉት። አጥፊን እንደጥፋቱ ዳኝቶ፣ ተበዳይን ክሶ በፍቅር፣ በሰላም፣ በአብሮነትና በወዳጅነት መሳሪያነት ለግጭት፣አለመግባባትና በደል እልባት ያስቀምጣል።

በሽምግልና በዳይም፣ ተበዳይም ኹለቱም አሸናፊዎች ናቸው ይባላል። እንደየ አካባቢው ባሕልና ወግ፣ እንደየ ጉዳዩ ቅለትና ክብደት ፣እንደየ ሃይማኖቱ አስተምህሮና ሥርዓት ተቃኝቶ ግጭትን አብርዶ ሰላምን ማንበር የባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት እሴት ነው።

ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት በማኅበረሰቡ ዘንድ ከእለታዊ ግጭት እስከ ታቅዶና ኾን ተብሎ የሚፈጠርን አለመግባባትና የጥል ውጤት ወደ ሰላም በመቀየር ወዳጅነትን እያወጀ ዘመናትን የተሻገረ አሻራ አሳርፏል።

የአማራ ክልል ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ማኀበር ሊቀመንበሩ ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከባሕላዊ እሴቶቿ የተናጠበች ሀገር እየኾነች ነው ይወቅሳሉ። ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓትን ያህል የድንቅ እሴት ባለቤት ኾና ሳለ በግጭት፣በብጥብጥና ቁርሾ የምትቸገር፣ ዜጎቿም በእኛና እነሱ ከፋፋይ ጥራዝ ነጠቅ ጽንፈኞች ሰለባ የኾኑባት ሀገር ኾናለች ይላሉ።

ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን እንደሚሉት ከውስጥም ከውጭም እኩይ አስተሳሰብን ባነገቡ አካላት የኢትዮጵያ ቀለም ፣ ድንቁ እሴቷ የሽምግልና ሥርዓት እንዲደበዝዝ ፣ከተቻለም እንዲጠፋ ተሰርቶበታል ነው ያሉት።
በተለይም በደርግ ሥርዓት ሶሻሊዝም ሲቀነቀን ከባሕልና ከእምነት ባፈነገጠ አካሄድ ከሸረሸራቸው የኢትዮጵያ እሴቶች መካከል ባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓት ተጠቃሽ ነው ይላሉ። ባሕላዊ እሴቶቻችን ታመዋል የሚሉት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን የማከም ተግባሩ ትኩረት እንደሚያሻው ነው በአጽንኦት የሚያሳስቡት።

“የአማራ ክልል የሽምግልና ሥርዓት ማኀበር” መቋቋም መቻሉን እንደጥሩ ጅምር ይጠቅሱታል። የማኀበሩ ተግባራዊ ዓላማው ደግሞ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት የተነጠቀውን ትኩረት ማስመለስ ነው ብለዋል።
ሌላው ለማኀበሩ መመሥረት ገፊ ምክንያት አንዱ በሀገሪቱ በሽምግልና መፈታትና የሰላም መንገድን የሚሹ ጉዳዮች መበራከትን ጠቅሰዋል።የፖለቲካ ጥገኝነት ላይ የተወሸቁ አካላት ባሕልንና ሥርዓትን ጎድተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
በእርግጥም ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል የሐሰት ሰነዶች እየተፈበረኩ የግጭትና የጥል ሰበዝን ሲመዙ፣ የሐሰት ትርክት እየተዜሙ ለግጭትና ብጥብጥ ምክንያት ሲኾኑ ኖረዋል። ይህን ሁሉ የታሪክን እዳ እልባት ለመስጠት ታዲያ ፖለቲካዊም ኾነ አሥተዳደራዊ መፍትሔ መስጠት በቂ ሊኾን አይችልምና ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ሚናውን መወጣት ይገባዋል ብለዋል።

ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓታችን ተሸርሽሯል ስንል ውጤቱን በመረዳት ነው የሚሉት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን፣ በሀገሪቱ የማይገራ ቡድንተኝነት፣አፈንጋጭ ብሔርተኝነት፣ለሕግና ሥርዓት የሚታበይ ትውልድ መፈጠሩ ማሳያ ነው ይላሉ። የሃይማኖት መሪዎችን፣የአባቶችን ምክርና ተግሳጽ ፣የሽማግሌዎችን ግልግል የማይሰማ ትውልድ በመኖሩ ከድጥ ወደ ማጥ የኾነ ነባራዊ ኹኔታ ተፈጥሯል ባይ ናቸው።
የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓታችን ጠንካራና በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅቡል፣ በመንግሥታዊ አሥተዳደሩና በፖለቲከኞቻችንም ዘንድ እምነት ቢኖረው ኖሮ ይላሉ ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን አስከፊው የሰሜኑ ጦርነት እልቂት ከማድረሱ በፊት ገላጋይ አይቸግረውም ነበር ወይም ገላጋይ ሽማግሌዎች ያደረጉት ሙከራ ባክኖ አይቀርም ነበር ይላሉ።

ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን “መንግሥት ለባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ምቹ መደላደል መፍጠር አለበት፣የሚደመጥ የሚታመን በመኾን አጋርነቱንም ማሳየት አለበት” ሲሉም ይገልጻሉ።
ግጭት እና አለመግባባትን በውይይት የመፍታት ጉዳይ፣በግልግልና መሸማገልን የመለማመድ ጉዳይ፤ ቤተሰብ ላይ መጀመርና መዳበር አለበት የሚሉት ደግሞ የ”ሰላም የበጎ አድራጎት ድርጅት” ምክትል ሥራ አስፈጻሚው መምህር አስቻለው መኮንን ናቸው። መምህር አስቻለው እንደሚሉት ለባሕሉ ፣ለወጉ ለሥርዓቱ ባይተዋር የኾነ ወይም ከእሴቱ ያፈነገጠ ትውልድ ለመፈጠሩ ምክንያት የሀገር ምሰሶው ቤተሰብ ላይ አለመሰራቱ ነው ይላሉ።
ትዳር ትልቅ ማኀበራዊ ተቋም፣ቤተሰብ የልጆቹ ብቻም ሳይኾን የሃገር ዋልታ ነው የሚባለው በትውልድ ቀረጻው ትልቁን ድርሻ ስለሚወስድ መኾኑን ያስረዳሉ።

በልጅነቱ ግብረገብነትን፣ሀገር ወዳድነትን፣በንግግር ውጤት ማምጣትን፣የሃሳብ የበላይነትን፣ ያልተለማመደ ግለሰብ ማኀበራዊ ነውር የማይገደው ለሕግና ሥርዓት የማይገዛ፣ከስብዕና ያልታረቁ ድርጊቶች ባለቤት መኾኑ አይቀርም ይላሉ።
ቤተሰብ ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነውና የግብረ ግብነት ልምምዱ፣ ትውልድ ቀረጻው፣ባሕልና ወጉ፣እሴት ግንባታው ፣ለትውልድም መሰረት መጣሉ ቤተሰብ ላይ መጀመር እንደሚገባ ነው የሚመክሩት። አስተዳደግ የበደለው ሀገር ያፈርሳል እና ትውልድ ግንባታው ትኩረት ያሻዋል ነው ያሉት። ይህ እውን እንዲኾን ታዲያ የሁሉንም ትብብራዊ ተግባር የሚያሻ ነው ብለዋል። ከትላንት እስከ ዛሬ ዓለምን ለጦርነትና ብጥብጥ የሚዳርጋት፣የኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሁሉ ምንጭ ሲተነተን አስተዳደግ ላይ ችግር ያለባቸው በትክክለኛው መንገድ ተቀርጸው ያላደጉ፣ የግብረገብነትና የስብዕና ችግር ያለባቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች በሚፈጥሩት ቀውስ ነው ይሉታል።

በኢትዮጵያም ዛሬ ላይ እንደ ሀገር አሳሰሰቢ ደረጃ ላይ የደረሰው የነጠፈ ስብዕና ውጤቱ ፣መሪና ተመሪውን በልኩ የማያግባባ፣ በሕግና በሥርዓት የማይዳኝ የመበራከቱን ምስጢር ቤተሰብ ላይ ይጥሉታል መምህሩ።
ለሚፈጠሩ አለመግባባቶችን፣ግጭቶችንና በደሎችን ለማረም በባሕል መሸምገልን፣ በሕግም መዳኘትን የሚቀበል ሞራላዊ አስተሳሰብ ማንበር የሚቻለው ከቤተሰብ፣ከትምህርት ቤትና ማኅበረሰብ ድረስ የሚከወኑ ልምዶችን ማዳበር ሲቻል ነው ብለዋል መምህሩ።

በእርግጥ ዛሬ ላይ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ቢደበዝዝ፣ ከልኩ ቢጎድል እንጂ ፈጽሞ ከሚናው የወጣ እሴት እንዳልኾነ ማሳያዎች አሉ ይላሉ። ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በተያዘው ዓመት ብቻ ወደ ፍርድ ቤት ከመጡ የክስ መዝገቦች ከ29 ሺህ በላይ የሚኾኑት በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት እልባት እንዲያገኙ ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱ እንደየ ጉዳዩ አለመግባባቶችን በእርቅ እንዲፈቱ ሃሳብ ሲያቀርብ ጉዳዩን በእርቅ ለመፍታት ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች በቀናነት መቀበላቸው እሴቱ ቢደበዝ እንጂ ዛሬም ድረስ ተስፋ የማይቆረጥበት መኾኑን ነው መረጃው የሚያስረዳው።

መንግሥት ፣ ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ኹሉ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቱ ሚናውን እንዲወጣ መሥራት አለባቸው ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን ይናገራሉ።

“የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሦስት ሽማግሌዎች የሚፈታን ችግር ሦስት ሻለቃ ጦር የሚልክ መንግሥት ለሰላም የራቀ ነው ” ነውና ብሒሉ መንግሥት ሕዝብ በሚቀበለው እሴቱ እንዲጠቀም እድል መስጠትን እንዲያስቀድም ገልጸዋል። ለሰላም መስፈን፣ለፍትሕ መረጋገጥና ለሕዝብ ደህንነት ሥራው መንግሥት ከባሕላዊ የእርቅና የሽምግልና ሥርዓቱ ጋር በይበልጥ ተባብሮና ተቀራርቦ ቢሰራ ጥቅሙ ለመሪም ለተመሪም ነው ብለዋል ።

ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን “ጦሳ የዘር ብዜትና ግብይት የኀብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን” በዛሬው ዕለት በይፋ ተመሰረተ።
Next articleበክምር ድንጋይ ከተማ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተመረቁ ነው።