ደሴ: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዮኒየኑ በዞኑ የሚገኙ የዘር ብዜት ማኅበራትን ኅብረት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሏል፡፡ ማኅበሩ በ7 ወረዳዎች የሚገኙ 14 የዘር ብዜት መስራች መሠረታዊ ማኅበራትን ያቀፈ ነው ተብሏል።
መነሻ ካፒታሉን 1 ሚሊዮን 820 ሺህ ብር በማድረግ የተቋቋመው ዩኒየኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለመግባት ከ 24 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገዋል ተብሏል። ይህም ለተለያዩ መጋዝኖች መሥሪያ፣ ለማበጠሪያ ማሽን ግዥና ለቢሮ ግንባታ ይውላል ተብሏል።
ማኅበሩ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ለአካባቢው ተስማሚና ገበያ ተኮር የኾነ ምርጥ ዘር በማቅረብ ፣ ግብአቶችን እና ቴክኖሎጅዎችን ለአባል ማኅበራት በማቅረብ የአባላትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።
አስተማማኝ የገበያ አገልግሎት በመፍጥር የአባላትን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል እንዲሁም በዞኑ ዘላቂ የምርጥ ዘር ስርጭት ማቅረብን ዓላማ ማድረጉም ተነግሯል።
በማኅበሩ ምስረታ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ሁሴን፤ የዩኒየኑ ምስረታ የምንጊዜም ችግራችን የኾነውን የምርጥ ዘር ስርጭት ክፍተትን እንደሚሞላ የታመነበት ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል 3 የዘር ብዜት ዩኒየኖች ይገኛሉ። በዚህ ዓመት ሁለት ተጨማሪ ዩኒየኖች መቋቋማቸውን የገለጹት የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ባለስልጣን አማካሪ አቶ ኃይለ ልዑል ተስፋ ናቸው፡፡
የዩኒየኖቹ መቋቋም የግብርና ሥራውን ከማሳለጥ አንጻር ፋይዳቸው የጎላ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
