
ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀሙሲት – መካነ ኢየሱስ መንገድን እስከ መጋቢት/2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ቢኾንም የወሰን ማስከበር ችግር አሁንም ፈተና መኾኑን የሀሙሲት – መካነ ኢየሱስ መንገድ ፕሮጀክት አማካሪ መሐንዲስ ገልጸዋል።
የሀሙሲት – መካነ ኢየሱስ መንገድ ፕሮጀክት የሀሙሲት – መካነ ኢየሱስ – ስማዳ መንገድ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው። የፕሮጀክቱ አማካሪ መሐንዲስ ዓባይነህ ዓለማየሁ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ከ 76 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ይሸፍናል፤ ”ኒግሽያ ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን” በተባለ ተቋራጭ ደግሞ አንደኛ ደረጃ የአስፋልት ሥራው እየተሠራ ይገኛል።
ለሥራው ከ1 ቢሊዮን 395 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል፡፡ የመንገድ ሥራው በገጠር 10 ሜትር ስፋት ሲኖረው በከተማ ደግሞ እንደ ከተሞች ኹኔታ ከ21 ሜትር እስከ 22 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት እንዳለው ነግረውናል፡፡
አማካሪ መሐንዲሱ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የካቲት 2012 ተጀምሮ የካቲት 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ነበር ወደ ሥራ የተገባው፡፡ ይሁን እንጂ በኮሮና ወረርሽኝ፣ በሲሚንቶ እና የነዳጅ እጥረት፣ በተለያየ ጊዜ የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ለመንገድ ሥራው ፈተና ነበሩ። በተለይም ደግሞ ከአጠቃላይ የመንገድ ሥራው ውስጥ ሰባት ከተሞችን የሚሸፍነው 17 ኪሎ ሜትር የወሰን ማስከበር ሥራ ባለመሠራቱ 59 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ሥራ ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 85 በመቶ ሥራው መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ችግሮች በተፈጠረው መዘግየት ምክንያት ተጨማሪ አንድ ዓመት ጊዜ መሰጠቱንም ነግረውናል፡፡ እስከ መጋቢት/2016 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎም ይታሰባል ነው ያሉት፡፡
የተጀመረው መንገድ በቀጣይ አንድ ዓመት ለማጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የካሳውን ክፍያ በፍጥነት በመክፈል በከተሞች የወሰን ማስከበር ሥራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ መሐንዲስ ዮሴፍ ወርቁ የአምበሳሜና አርብ ገበያ ከተሞች የካሳ ክፍያ መከፈሉን ገልጸዋል።
የሌሎች ክተሞችን የካሳ ክፍያ የተመለከተ ሰነድም ተሠርቶ ለኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ቢላክም የካሳ ክፍያው በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ነው ያብራሩት። በተለይም ደግሞ ከየካቲት/2015 ዓ.ም ጀምሮ የካሳ ክፍያ ለጊዜው እንደ ሀገር እንዲቆም መደረጉንም አንስተዋል። በቀጣይ ለጊዜው እንዲቆም የተደረገው የካሳ ክፍያ እንደተፈቀደ ወደ ሥራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
