“ኢትዮጵያ አካታች የትምህርት ስርዓትን በመከተል ሁሉም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራች ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

67

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ አካታች የሆነ የትምህርት ስርዓትን በመከተል በዘርፉ ሁሉም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትምህርት ትብብር ድርጅት የመጀመሪያ ልዩ ጉባዔ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ የድርጅቱ ዓላማዎች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።

ትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ዓለምን በበጎ መልኩ ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዓለም እያጋጠማት ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ብዝኃነትን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የመፍትሄ አማራጮች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት የድርጅቱ የወቅቱ ፕሬዝዳንትና የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ፥ የድርጅቱ ስም በጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ወደ “የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት የትብብር ድርጅት” መቀየሩን ጠቅሰዋል።

የጉባዔው ዓላማ በሀገራቱ መካከል መልከ ብዙ ትብብር ለመፍጠር እንዲሁም ፍትሀዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም መፍጠር ነው ብለዋል።

የተቋሙ ዋና ፀሐፊ ኢትዮጵያም ተቋሙን በዋና መቀመጫነት ለመቀበልና ለስኬቱ ያሳየችው ቁርጠኝነት የሚመሰገን ነው ብለዋል።

ኢቢሲ እንደዘገበው ላለፉት ሁለት ቀናት በሚኒስትሮች ደረጃ ሲካሄድ የቆየው ልዩ ጉባዔ፤ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት በአባል ሀገራት መሪዎች ደረጃ ውይይት የሚደረግበት ይሆናል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በትምህርት ላይ የምንሠራቸው ሥራዎች ወጣቶቻችን በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleአሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥስት ክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ ክልከላ ማንሳቷን አስታወቀች።