
ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (ኦኢሲ) በአዲስ አበባ እያካሄደ ባለው የመጀመሪያው ልዩ ጉባኤ ላይ እየሳተፉ ነው።
ላለፉት ሁለት ቀናት በሚኒስትሮች ደረጃ ሲካሄድ የቆየው ልዩ ጉባኤ የድርጅቱ አባል አገራት መሪዎች ስብሰባ ዛሬ ተጀምሯል።
መሪዎቹ ለሁለት ቀናት ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤው የደቡብ ለደቡብ ትብብር ማዕቀፍን ለማጠናከር ፣ በትምህርቱ ዘርፍ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት መሰረተ ያደረገ አዲስ የባለ ብዙ ወገን ትብብር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የፖሊሲ ውይይቶች እና ክርክሮች እየተደረጉበት ይገኛል።
ትናንት በልዩ ጉባኤው ሁለተኛ ቀን ውሎ የድርጅቱ አባል አገራት በውይይታቸው ተቋሙ ካስቀመጠው ተልዕኮ አንጻር ሊሳካ የሚችል የስም ስያሜን በተመለከተ መክረዋል።
በዚሁ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤው ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ስያሜው ደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት ትብብር ድርጅት በሚል እንዲቀየር ውሳኔ አስተላልፏል።
የድርጅቱ የወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የፕሬዝዳንትነት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ለኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ኃላፊነታቸውን ማስከረከባቸው ይታወቃል።
ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (ኦኢሲ) እ.አ.አ ጥር 2020 የተቋቋመ ሲሆን ከአፍሪካ ፣ እስያ፣ ፓሲፊክ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን እና የአረቡ ዓለም ሀገራትን በአባልነት ያቀፈ ነው።
ድርጅቱ ሚዛናዊ ፣ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ስርዓት በመዘርጋት በእኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት ላይ የተመሰረተ ልማት ማምጣትን አላማ አድርጎ እየረራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ኢዜአ እንደዘገበው ኢትዮጵያ የተቋሙ መስራች አባል እና ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ ናት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
