“ጠለምት–ስለማንነት መሥዋእትነት የተከፈለበት”

93

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ስለማንነት እልፍ መሥዋዕት ተክፍሎበታል፣ ደም ፈስሶበታል፣ አጥንት ተከስክሶበታል፣ አያሌ የመከራ ጊዜያት ታልፎበታል፡፡ ማንነታችን ያሉ ተገድለዋል፣ እውነት የተናገሩ፣ ታሪክ እየጠቀሱ የመሰከሩ ተሳደዋል፣ ታስረዋል፣ ብዙዎችም የት እንደገቡ ሳይታወቅ ጠፍተው ቀርተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የኾነው ለማንነት፣ ለእውነት፣ ለነጻነት ነው፡፡

በደል ያልተገኘባቸው እንደበደለኛ ተቆጠሩ፤ ክፋት ያልተገኘባቸው እንደ ክፉ ተወገሩ፤ አማራ ነን በማለታቸው ብቻ የመከራ ጽዋን ተቀበሉ። በግፍ ሰይፍ ተገድለው ያለ ሥርዓት ተቀበሩ፡፡ በዚያች ምድር ማንነታችንን አንተውም፣ እውነታችንን አንጥልም ያሉ ሁሉ የመከራ ዶፍ ወርዶባቸዋል፡፡ ዳሩ ከአባት የወረሱት ጀግንነት፣ ጽናት፣ አልሸነፍም ባይነት አላቸውና በመከራ ጸንተው ኖሩ፡፡

ለአሳዳጆቻቸው አንገታቸውን አልደፉም፣ በጠላቶቻቸው አልተሸነፉም፣ በጨለማ አብርተው፣ በአንድነት ጸንተው፣ እንደ አለት ጠንክረው፣ የገፏቸውን ጣሏቸው፣ ያሳደዷቸውን፣ ያለ ማንነት ማንነት እንስጣችሁ ያሏቸውን፣ ያለ ባሕል ባሕል እንጫንባችሁ ያሏቸውን ድል ነሷቸው እንጂ፡፡

ታሪክ አዋቂዎችን ገድለው የጨረሱ ሲመስላቸው ወጣቶች የአባቶቻቸውን ታሪክ እያስታወሱ ይገጥሟቸዋል፤ ማንነታቸውን አጠፋናቸው ሲሉ በማንነታቸው ጸንተው ያገኟቸዋል፣ የጀግና ልጅ ጀግና፣ የብልህ ልጅ ብልህ ነውና የወላጆቻቸውን ማንነት እና እውነት አይጥሉም፡፡ ልጆቹ እንደ አባቶቻቸው ለጠላት አይቀመሱም፣ ከድል ላይ ድል ይደራርባሉ፣ ነጻነታቸውን በጀግንነታቸው ያጸናሉ እንጂ፡፡

በጠለምት ምድር አያሌ በደሎች ተፈጽመዋል፡፡ በማንነታቸው ብቻ ፍርደኛ የተባሉ አማራዎች በጅምላ ተቀብረዋል፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀልም ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ይህም ለዓመታት የቀጠለ ወንጀል ነበር፡፡

የአካባቢው ተወላጅና ታሪክ አዋቂው ስለሺ ንጉሤ ደስታ በጠለምት ላይ ስለደረሰው ግፍና ለዓመታት ስለነበረው ተጋድሎ ሲነግሩኝ የወያኔ ሰዎች ወደ ጠለምት ተሻግረው ያለ ግዛታቸው ግዛታችን፣ ያለ ማንነታቸው ማንነታችን ማለት ጀመሩ፡፡ ጠለምት ሲገቡ ሰው የሚያከብራቸውን፣ የሚወዳቸውን፣ ታሪክ የሚያውቁ፣ የተጣላን የሚያስታርቁ፣ እንደ ዋርካ የሚታዩ ታላላቅ የታሪክ ሰዎችን እና ባላባቶችን አሠሯቸው፡፡ የሕወሃት ሰዎች ወደ ትግራይ ወሰዷቸው፣ የሚገድሏቸውን ገደሏቸው፣ አካላቸውን አጎደሏቸው፣ ሌሎችንም አሳደዷቸው ነው ያሉኝ፡፡

ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ የሀገር ባላባቶች እና ታሪክ አዋቂዎች እየተፈለጉ ይሳደዱ እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ ብዙዎችን ደብዛቸውን አጠፏቸው፡፡ አንዳንዶችን በርካታ ዓመታትን አሥረው ለቀቋቸው፣ ሲለቀቁም የጤና እክል ደርሶባቸው ስለነበር ብዙም ሳይቆዩ ያለፉም አሉ ነው ያሉኝ፡፡

የእርሳቸው ዘመዶችም ብዙ ግፍና መከራ እንደደረሰባቸው ነው የነገሩኝ፡፡ ወጣቱን ትውልድ ታሪክ ይነግራሉ የሚሏቸውን ሁሉ የማጥፋት ሥራ የመጀመሪያው ሥራቸው እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ የወያኔ ሰዎች ይሄን ሲያደርጉ የጠለምት ጀግኖች ከፋኝ ብለው ተነሱ፡፡ በማንነታቸው፣ በታሪካቸው እና በሕልውናቸው ላይ ከመጣው ጋር ገጠሙ፡፡ ይህም ተጋድሏቸው ለቀናት፣ ለሳምንታት፣ ለወራት ብቻ አልነበረም ለዓመታት ዘለቀ እንጂ፡፡

ለዓመታት በዘለቀው ተጋድሎም ብዙ ጀግኖች መሥዋእት ከፍለዋል ነው ያሉኝ ታሪክ አዋቂው አቶ ስለሺ፡፡ በርካታ ታሪክ አዋቂ ሰዎች ለማንነታቸው መከራን ታግሰዋል፣ መሪር ሞትንም ቀምሰዋል፡፡ ቁጥራቸው የበዛ የጠለምት አማራዎች እንዲፈናቀሉ ተደርገዋልም ነው ያሉት፡፡

ዓይናቸው እያየ አማራነታቸውን ሽሮ ሌላ ማንነት ሊሰጣቸው፣ ታሪካቸውን ሊቀይርባቸው የመጣውን ሥርዓት ልናይ አንችልም ዝምም አንልም በማለት አሻፈረኝ ብለው ታግለውታልም ነው ያሉኝ፡፡
ልጆቻቸው ያለ ታሪካቸው ታሪክ ሲነገራቸው፣ ያለ ማንነት ማንነት ሲሰጣቸው፣ የአማራን ሥነ ልቦና ትተው እንዲያድጉ ሲደረጉ አሻፈረኝ፣ ይሄን ከማየትና በዚህ ሥርዓት ከመገዛት ሞት ይሻለናል ብለው በረሃ የወረዱት ብዙዎች መኾናቸውንም ነግረውኛል፡፡

የጠለምት ሕዝብ ለዓመታት የአማራነት ማንነቱን እንዲጥል፣ ባሕልና ቋንቋውን እንዲረሳ ሲደረግ መኖሩንም ያስታውሳሉ፡፡ የጠለምት ጀግኖች እና ታሪክ አዋቂዎች ለዓመታት በዘለቀው ተጋድሏቸው ወጣቱ ታሪኩን እንዲያውቅ፣ ባሕሉን እንዲጠብቅ፣ ማንነቱን እንዲረዳና ለማንነቱ እንዲታገል ሲያደርጉ መኖራቸውንም ነግረውኛል፡፡ የጠለምት ማንነት ከአማራ ሕዝብ መነጠል እንደማይቻል፣ ሊቀየር እንደማይችል ማስተማራቸውን ነግረውኛል፡፡

የጠለምትን የአማራነት ማንነት ሲያስተምሩ የኖሩ ታሪክ አዋቂዎች ምሥጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ የጠለምት ሕዝብ አማራ ነኝ ሲል ያለማንነቱ ማንነት እንዲቀበል ግፍ ሲደርስበት እንደኖረም ነግረውኛል፡፡ ጠለምት አማራ ነን፣ በአማራነታችን አትምጡብን እንጂ አማራ እንኹን አለማለቱንም ነግረውኛል፡፡ የጠለምት ሕዝብም በተደጋጋሚ “አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም” እያለ በአደባባይ ለዓለም አሳይቷል፡፡

የጠለምት ሕዝብ የአባትና የእናቱን ማንነት አክብሩልኝ እያለ በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቅ ጀግና፣ ፍትሕ አዋቂ፣ ሰላም ፈላጊ ሕዝብ ነውም ብለውኛል፡፡ እንደ ሕዝቡ ሰላም ወዳድነት እና ፍትሐዊ ጥያቄ ግን አፋጣኝ መልስ አልተሰጠውምም ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ለዚህ ኩሩና እውነተኛ ሕዝብ ጥያቄውን ሊመልስለት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ጠለምት ባሕሉ አማራ፣ ሥነ ልቦናው የአማራ፣ ታሪኩ የአማራ፣ ቋንቋው አማርኛ ነውም ብለዋል፡፡ ጠለምት ጥንትም፣ ዛሬም ነገም ከአማራ መነጠል አይቻልም ነው ያሉኝ።

የጠለምትን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ከመመለስ ባሻገር ለዓመታት ለደረሰበት ግፍ፣ መሳደድ፣ ግድያ እና የሥነ ልቦና ጫና ካሳ እና ፍትሕ ያስፈልገዋልም ብለዋል፡፡ በጠለምት ሕዝብ ላይ ግፍና በደል ያደረሱ አካላትም ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

መንግሥት የጠለምትን ታሪክ፣ ሥነ ልቦና፣ ማንነት፣ ባሕልና ቋንቋ በማየት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባልም ነው ያሉት፡፡ የጠለምት ሕዝብ ስለ አማራዊ ማንነቱ መሥዋእት ከፍሏል፣ ከዚህ በኋላ ማንነቱን ለማንም አሳልፎ አይሰጥም። የጠለምትን የአማራ ማንነት ምላሽ አለመስጠት በአካባቢው ሰላም እንዳይፈጠር መሻት እንደኾነም ነግረውኛል፡፡

ለዓመታት መሥዋእት የከፈለው የጠለምት ሕዝብ ከእንግዲህ በኋላ ያለ ማንነቱ ይኖራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነውም ብለዋል፡፡

የጠለምት፣ ወልቃይትና የራያ ጥያቄ የመላው የአማራ ሕዝብ እና ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው ያሉት ታሪክ አዋቂው አቶ ስለሺ የአማራ ሕዝብ በአንድነት ማንነቱን፣ ታሪኩን እና ባሕሉን ማስጠበቅ አለበት ነው ያሉት፡፡ አንድ የኾነን ሕዝብ የሚደፍረውና የሚተነኩሰው እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ማንነቱን እና ታሪኩን ሊያሳጣው የሚፈልገውን የትኛውንም ኀይል በአንድነት መታገል አለበትም ብለዋል፡፡

አንዳንድ ምዕራባዊያን ግፍ የደረሰበትን የአማራን ሕዝብ ከመደገፍ ይልቅ ግፍ አድራሾችን እንደሚደግፉም አንስተዋል፡፡ ይህም ጠንካራ ሕዝብና ሀገር እንዳይኖር ስለሚፈልጉ መኾኑን ነው ያስረዱት።

አማራው መሳደዱን፣ መፈናቀሉን፣ መሞትና መሰቃየቱን አይቶታል ከዚህ በኋላ ይህ እንዳይደገም በአንድነት መቆምና በአንድ ልብ መደራጀት ይጠበቅበታልም ብለዋል። ለኢትዮጵያ አንድነት የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለጠለምት፣ ለወልቃይትና ለራያ ጥያቄ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ከባርነት ነጻነት ይሻላል፣ ለነጻነት የሚደረገው ትግል እና የሚከፈለው መሥዋዕትነት ክብር ነው፣ በታሪክ ያደምቃል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብ ሊመጣ የሚችለውን ችግር ለመመከት በአንድነት መቆም አለበትም ብለዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ በታሪክም፣ በሥነ ልቦና፣ በባሕል፣ በሃይማኖት ከአማራ ሕዝብ የበለጠ የሚቀርበው እንደሌለ በማመን ፖለቲከኞች እስካሁን የሠሩትን ስህተት እና ያደረሱትን በደል እንዳይደግሙት ሊታገላቸው ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ጠለምት ስለ አማራ ማንነት መሥዋእት የተከፈለባት፣ መከራ የታየባት፣ ጀግኖች አያሌ ጀግንነትን የሠሩባት፣ በጀግንነትም ድል የመቱባትና ነጻነታቸውን የተቀዳጁባት ምድር ናት ነው ያሉት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠና በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት የመጀመሪያ ልዩ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው ።