የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠና በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ነው።

87

ጎንደር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ነው ስልጠናውን እየሰጠ የሚገኘው፡፡ የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ነጋ ይስማው ከማኅበረሰቡ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ተጠቃሚነት ፍላጎት ከፍ ማለት ጋር ተያይዞ ተመጣጣኝ ምርት እንዲኖር ለማስቻል ስልጠናው እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍም የሌማት ትሩፋት እቅዶችን ለማሳካት የሚያስችል መኾኑን አስታውቀዋል። በዘርፉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መኾኑን ያብራሩት ኀላፊው የተሻለ ሥራ መሥራት መቻሉን ገልጸዋል። መስኩ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀይሉ አለሙ በጎንደር ከተማ በእንስሳት ሀብት ሥራ ላይ ልዩ ልዩ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል ። አሁንም ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡ ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያም ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው በእንስሳት ሀብት ሥራ ተጠቃሚ መኾን መቻላቸውን አስታውቀዋል።

የአሰልጣኞች ስልጠና የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ የሌማት ትሩፋት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሥራው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ጎንደር ከተማ በዘርፉ ለመሥራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

እየተሰጠ የሚገኘው የእንስሳት ሀብት ልማት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠና ከዛሬ ሰኔ 22/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ሲኾን በስልጠናው የማዕከላዊ፣ የሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ባለሞያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሁሉም ዞኖች ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ሕዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል” ትምህርት ቢሮ
Next article“ጠለምት–ስለማንነት መሥዋእትነት የተከፈለበት”