“በሁሉም ዞኖች ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ሕዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል” ትምህርት ቢሮ

80

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መማር ማለት የባህሪ ለውጥ ማምጣት ማለት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን አዘውትረው ይናገራሉ፡፡ ትምህርት የማንኛውም ማሕበረሰብ መሠረታዊ የግንባታ ሂደት ነው፡፡ ውስብስብ የሆነው የሰው ልጅ እና የተፈጥሮ መስተጋብር ምስጢር የሚፈታው በትምህርት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ትምህርት የሰውን ልጅ አዕምሮ በመሳል እና በመቅረጽ ረገድ የሚስተካከለው የለም፡፡

ኢትዮጵያ ከትምህርት ጋር ያላት ቅርርብ እና ትውውቅ ዘመንን ይሻገራል፡፡ ጥንታዊው ሀገር በቀል የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ራስን ማወቅ፣ ግብረ ገብነት እና ችግር ፈቺ እንደነበር ይታመናል፡፡ ብራና እና ቀለምን አዋደው ትምህርትን ከቤተ እምነት እስከ ቤተ መንግሥት ያስተናበሩት ኢትዮጵያዊያን “የቀለም ቀንድ” የሚል መጠሪያ እስከማግኘት ደርሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ፈር ቀዳጅ ናት ባትባልም ብዙ ውጣ ውረድ ያለፈ የትምህርት ተሞክሮ ግን አይጠፋትም፡፡ ከ1950ዎቹ ገደማ ጀምሮ የመስፋፋት ምልክቶችን እያሳየ የመጣው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት እስካሁን ለዘለቀው ክፉና በጎ ተፅዕኖ ድርሻው ላቅ ያለ ነው፡፡ ከጀኔራል ዊንጌት እስከ ወይዘሮ ስኂን፤ ከተግባረ ዕድ እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤቶች የዘመናዊ ትምህርት ምልክቶች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይም የጀኔራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ እና በስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን አሰባስቦ በማስተማር ገናና ሥም እና ተፅዕኖ ነበረው፡፡ የጀኔራል ዊንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በልዩ እንክብካቤ አጠናቀው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እስከ ውጭ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት እድሎች ፈር ቀዳጆች ነበሩ፡፡ አሁንም ድረስ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዋር ከሚዘውሩት የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የጀኔራል ዊንጌት ተማሪዎች ተፅዕኖ እንዳለበት ይታመናል፡፡

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የተለየ የትምህርት አቀባበል ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች ማሰባሰብ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በተለየ መልኩ መሥራት እና መቅረጽ እንደሆነ ይታመናል ያሉን የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ናቸው፡፡ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርታቸው እንዲሰጡ፣ ለምጣኔ ሃብታዊ ውስንነቶች እንዳይጨነቁ፣ የሀገር እና ሕዝብ ውለታን እንዲያስታውሱ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ፋይዳቸው የጎላ ነው ይላሉ፡፡

አሁን ድረስ በዘለቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ድርሻ አለበት የሚሉት ፕሮፌሰር መንገሻ በቅርብ ክትትል የመጻዒዋን ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በበጎ የሚተልሙ ልጆችን ማፍራት ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡ ሀገሪቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋያ አፍስሳ መሥራት ያለባት ዘርፍ ትምህርት ነው፤ ትኩረቱም ሰውን መፍጠር የሚችል የትምህርት ሥርዓት ለማንበር የሚረዳ እና የተጠና መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት የትምህር ቢሮ የቀጣዮቹ 10 ዓመታት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ገልጸዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በባለሃብቶች፣ የዲያስፖራው ማሕበረሰብ እና በሲቪክ ተቋማት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መልካም ጅምሮች አሉ፡፡ የሕዝቡን እና የሲቪክ ማሕበራትን መልካም ጅምር አጠናክሮ ለመቀጠል የክልሉ መንግሥት ቁርጠኝነት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በትምህርት ሴክተሩ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል “የዜግነት አገልግሎት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት” የንቅናቄ መርሐ ግብር በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል፡፡ “በሁሉም ዞኖች ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ሕዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ጌታቸው በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በገንዘብ፣ በእውቀት እና በሙያ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መልካም ጅምሮች ይታያሉ ያሉት አቶ ጌታቸው ተሞክሮዎችን በማስፋት ሁሉም ተቋማት ጉዳዩን በኅላፊነት እንዲይዙ ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የትምህርት ሥርዓት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በተለያዩ ዘርፎች ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እየሰራ ነው፡፡ የልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚችሉ አቅም ያላቸው ተማሪዎች የሚፈልቁበት በመሆኑ በልዩ ትኩረት ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ትምህርት ቁልፉ መሳሪያ መሆኑ አያጠያይቅም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው የክልሉ መንግሥት በልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ኅላፊነቱ ላቅ ያለ ነው ብለዋል፡፡

የልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ፕሮጀክት ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው አልማን ጨምሮ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ከሲቪክ ማሕበራት የተቀናጀ ተሳትፎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ባለሃብቱ እና ሕዝቡ ከፍተኛ እርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የፀጥታ መድረክ በቻግኒ ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleየእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠና በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ነው።