
ቻግኒ: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ውይይቱን እየመሩ የሚገኙት የሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ሲኾኑ በመድረኩም የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዞን እና የወረዳ የፀጥታ መዋቅር አመራሮች፣ የመተከል ዞን አመራሮች፣ የምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አመራሮች፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን እና ሌሎች አካላትም ተሳታፊ ናቸው።
የአማራ ክልል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጎራባች ወረዳዎች በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ በየጊዜው መወያየታቸው በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የጎላ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ተናግረዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ አብዮት አልቦሮ በበኩላቸው ዞን ከዞን ጋር፤ ወረዳ ከወረዳ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ሰላም ላይ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት። በዳንጉር እና ጃዊ ወረዳዎች አካባቢ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
ውይይቱ ላይ የሁሉም ዞን አመራሮች አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡ ሲኾን በቀረቡት ሃሳቦች ምክክር ተደርጎ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
