በጤና ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለመተግበር እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።

47

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ሥርዓት ትግበራን አስጀምሯል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) ተገኝተው ትግበራውን አስጀምረዋል። በክልሉ ጤና ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለመተግበር እየተሠራ መኾኑን ዶክተር መልካሙ ተናግረዋል። በክልሉ የደሴ እና የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች የዚህ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ተጠቃሚዎች መኾናቸውንም አንስተዋል። በቀጣይም በርካታ የጤና ተቋማት ከቆየው የካርድ ሥርዓት ወጥተው ወደ ኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ልውውጥ አሠራር እንዲገቡ ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት።

በጤና ተቋማት ተግባራዊ የሚደረገው የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ልውውጥ ዘዴ ከወረቀት የተላቀቀ፣ የሰው ኀይል ፍጆታን የሚቀንስ እና አላስፈላጊ ወጭንም የሚያስቀር ነው ብለዋል። ታካሚዎች ካርድ ለማውጣት በመቆም የሚያባክኑትን ጊዜ ስለሚቀንስ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላልም ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አስማማው ሞገስ በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ልውውጥ ዘዴው ቀደም ሲል በባሕር ዳር እና ሽንብጥ ጤና ጣቢያዎች መጀመሩን ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ በሃን ጤና ጣቢያ ተግባራዊ ተደርጓል። ታካሚዎች ወደ ጤና ጣቢያው ከገቡበት ሰዓት ጀምሮ ታክመው እስከሚወጡ ድረስ ከወረቀት ንክኪ ነጻ ኾነው በቴክኖሎጅ በመታገዝ ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል ተብሏል።

የሃን ጤና ጣቢያ ካርድ ክፍል ባለሙያዋ አስንቃ ሙላው በጤና ጣቢያው በቀን እስከ 3 ሺህ የወረቀት ካርድ ይንቀሳቀስ እንደነበር ገልጸዋል። ካርዱን ከመደርደሪያ ላይ ለመፈለግ ከፍተኛ ጊዜ እና ጉልበት ይጠይቅ ነበር። ለካርዱ ማከማቻ የሚውል ሰፊ ቦታ ይፈልግ እንደነበርም ባለሙያዋ ተናግረዋል። አሁን ላይ ተግባራዊ የኾነው የኤሌክትሮኒክስ አሠራር ይህንን ሁሉ የሚቀርፍ እና ለታካሚዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስለመኾኑም ነው ያስረዱት።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመኾን ጥያቄ ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next articleየአማራ ክልል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የፀጥታ መድረክ በቻግኒ ከተማ እየተካሄደ ነው።