ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመኾን ጥያቄ ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

104

አዲስ አበባ: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት ባለፉት ጊዚያት የተፈጠሩ ችግሮችን በማስተካከል የዲፕሎማሲውን ግንኙነት ማስተካከል ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ በጦርነቱ ምክንያት በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሽግግር ፍትሕ ለማካሔድ መንግሥት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ይህም የሀገር ውስጥ ችግሮችን ከማስተካከል ባለፈ የዲፕሎማሲ ገጽታ ግንባታ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት የማስተካከል እድል እንደሚኖረው አንስተዋል።

እንደ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጻ የጅቡቲ የፐብሊክ የዲፕሎማሲ ቡድን 112 አባላትን ይዞ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ብለዋል። ጉብኝቱም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲኖር የሚጠቅም መድረክ ይኾናል ብሏል።

የአፍሪካ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ባደረጉት ስብሰባ በዓባይ ውኃ ላይ ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። የላይኛው የተፋሰስ ሀገራት የናይል ውኃ ጉዳይ የደህንነት እና የልማት ጉዳይ መኾኑን መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ ውኃውን መሰረት ያደረጉ የጋራ ልማት ላይም መሥራት እንደሚገባ፣ የህዳሴ ግድብንም የተፋሰሱ ሀገራት የጎበኙ ሲኾን ስለግድቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረግ ተችሏል ተብሏል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመኾን ጥያቄ አቅርባለች ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አምባሳደር መለስ ኢትዮዮጵያ ጥያቄ ማቅረቧን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የተመድ እና የአፍሪካ ኅብረት መስራች አባል ሀገር በመኾኗ ዓለም አቀፍ ድርጅት የመቀላቀል ብቻ ሳይኾን የመመስረትም ልምድ አላት ነው ያሉት፡፡ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ኹኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚያስከበር የዲፕሎማሲ መንገድን በመከተል ጥያቄ አቅርባለች ብለዋል፡፡ በዚህም በአግባቡ ጥያቄያችን መልስ ያገኛል ብለን እናምናለን፣ ጥያቄያችን በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ እንከታተላለን ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ሁሉንም የሀገራችን ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲኾኑ እንሠራለን።” ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
Next articleበጤና ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለመተግበር እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።