
አዲስ አበባ: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ሁሉንም የሀገራችን ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን በየጠበቁ እንዲኾኑ እንደሚሠሩ ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ እሁድ ሰኔ 25/2015 የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚካሄደው መርሐ ግብሩ በይፋ ይጀመራል፡፡
ባለፉት ዓመታት ለትምህርት ዘርፉ በተሰጠው አነስተኛ ትኩረት የትምህርት ዘርፉ ስብራት ገጥሞታል ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ ይህንን ለማሻሻል ሥራዎች በመከወን ላይ ናቸው ብለዋል።
በተለይ በተሰጡ ፈተናዎች በተገኙ ውጤቶች የትምህርት ሥርዓቱ እጅጉን መጎዳቱን ያነሱት ሚኒስትሩ ችግሩን መቀልበስ እንዳለብን አስበን እየሠራን ነው ብለዋል። ከዚህ ባሻገር በተሠራ ጥናት ለችግሩ ስፋት የትምህርት ቤቶች ጥራትና ደረጃ ትልቁን ቦታ ይይዛል ተብሏል።
የ56 ሺህ ትምህርት ቤቶችን ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በመንግሥት አቅም ከ30 እና 40 ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተገማች ነው ተብሏል።
ተቋማቱን ለማሻሻልም ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሁሉንም የማኀበረሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ የማሻሻል ሥራዎች ይጀመራሉ ተብሏል፡፡ ዕውቀት፣ ሀብትና ጉልበት ያለውን ሁሉ እናሳትፍበታልን ብለዋል ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ። ምናልባትም ይህን ማድረግ ከቻልን የነገ ትውልዳችን ከየትኛውም የዓለም ክፍል ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ መኾን የሚችሉበትን አቅም መፍጠር ያስችለናልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!