“በአማራ ክልል ከበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከእቅድ በላይ ምርት ይጠበቃል” ግብርና ቢሮ

110

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የምርት ዘመን በክልሉ ከበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከ4ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያስታወቀው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አግደው ሞላ ለአሚኮ እንደተናገሩት በ2015 ዓ.ም የምርት ዘመን በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የተገኘው ዝናብ ለሰብል ልማት ምቹና ከበቂ በላይ ነበር።

በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በሽፋን የተሻለ ምርታማነት የሚያስገኝ ቡቃያ ታይቷል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

በክልሉ በበልግ ዝናብ አብቃይ አካባቢዎች 218 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ ከእቅድ በላይ 230 ሺህ ሄክታር መሬት መሸፈኑን ነው አቶ አግደው የተናገሩት። ከዚህም በምርት ዘመኑ ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል። በወቅቱ በተገኘው ከበቂ በላይ የበልግ ዝናብ እና ተስማሚ ወቅታዊ የአየር ኹኔታ ከእቅድ በላይ ምርት እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

በክልሉ ከበልግ ወቅት አብቃይ አካባቢዎች ደቡብ ወሎ ዞን ተጠቃሽ ነው። የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ይመር ሰይድ እንዳሉት ዞኑ በዘንድሮው የበልግ ወቅት በቂ ዝናብ ማግኘት ችሏል።

በደቡብ ወሎ ዞን በ12 ወረዳዎች 101 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈን መቻሉንም ገልጸዋል። አቶ ይመር እንዳሉት ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሾ፣ ቦሎቄ፣ ምስርና ሌሎችም የጥራጥሬ ሰብሎች በዞኑ በስፋት ይመረታሉ። 80 በመቶውን የበልግ ወቅት ዝናብ ምርት የሚሸፍነው ገብስ እንደኾነም ቡድን መሪው ተናግረዋል።

እንደ ደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ መረጃ በዞኑ 1ሚሊዮን 6መቶ ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ተብሏል። እቅዱን ለማሳካትም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ቡድን መሪው።

ወቅቱ የበልግ ወቅት ሰብል የሚሰበሰብበት መኾኑን የተናገሩት አቶ ይመር ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዞኑ 5ሺህ ሄክታር መሬት ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል።

አርሶ አደሮች የግብርና ባለሙያውን ሙያዊ ሃሳብ እና ወቅታዊ ኹኔታውን እየተረዱ ሰብልን በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ከክርስቲያን ሪሊፍ ጋር በመተባበር ከ16 ሺ በላይ መፅሐፍትን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረገ።
Next article“በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ሁሉንም የሀገራችን ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲኾኑ እንሠራለን።” ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ