ደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ከክርስቲያን ሪሊፍ ጋር በመተባበር ከ16 ሺ በላይ መፅሐፍትን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረገ።

51

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረታቦር ዩኒቨርስቲ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው”ክርስቲያን ሪሊፍ” ከተሰኘ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር 16ሺ 255 መፅሐፍትን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርጓል።

መጽሐፎቹ ለ37 ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ተደርገል።

ዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው ድጋፉ የተገኘው በዩኒቨርስቲው ባሉ ልበ ቀና ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ድጋፍ ከሚያገኙ ወኪሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ የተገኘ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ዩኒቨርስቲያችን በከተማ አስተዳደሩ እና በዞኑ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ከትምህርት ተቋማት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርስቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መንበሩ ተሾመ ፤ ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር በተጨማሪ መጠነኛ ሀብትና ጊዜን በመጠቀም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በዕለቱ የተደረገው ለትምህርት ቤቶች የመጽሐፍት ድጋፍ ትምህርት ቤቶች ባቀረቡት ጥያቄና ትምህርት መምሪያው ባቀረበው አስተያየት መሰረት ድጋፉ የተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል ።

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተሩ ዶክተር ታደሰ ዋለልኝ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተለያየ የሙያ ስብጥር ያላቸው ምሁራን ያሉበት ተቋም በመሆኑ በአካባቢው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የቁሳቁስና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ ለሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት የተሰጠ መሆን ተናግረዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሃላፊ እና የትምህርት ቤት ተወካዮች በተሰጠው አስተያየት ዩኒቨርስቲው በአካባቢው ማኅበረሰብ የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ የትምሕርት የጥራትን ማስጠበቅን በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን ገልፀው፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር በዞኑ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን በመርዳት ሊኾን ይገባል” የሰሜን ጎንደር ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት
Next article“በአማራ ክልል ከበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከእቅድ በላይ ምርት ይጠበቃል” ግብርና ቢሮ