
የውጭ ሀገራት ወገኖችን በአክሲዮን ሽያጩ ለማሳተፍ የብሔራዊ ባንክን የአሰራር ማስተካከያ እየጠበቀ መሆኑን የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር አደራጅ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
ባንኩ በክልሉ ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠርን፣ አስተማማኝ የቁጠባ፣ የብድር እና የባንክ አገልግሎት መሥጠትን ዓላማ አድርጎ ነው የተመሠረተው፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩን ፋይዳዎች እና የዳያስፖራውን ተሳትፎ የተመለከተ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ወገኖች ጋር ዛሬ ምክክር ተካሂዷል፡፡ በኮሎምበስ—ኦሀዮ ከሕዝባዊ ውይይቱ አስቀድሞ ከልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር በተደረገው ምክክር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖች ተሳትፎ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባለፈ የዕውቀት እና የልምድ ድጋፍ ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ በተለይም ለአብመድ እንደተናገሩት ባንኩን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችለው 5 መቶ ሚሊዮን ብር ካፒታል የተሰበሰበ ቢሆንም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖችን ለማሳተፍ ሲባል ላልተወሰነ ጊዜ የአክሲዮን ሽያጩ ሊራዘም ይችላል፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ባንኩ የውጭ ሀገራት ዜጎች በአክሲዮን ግዥው እንዲሳተፉ የሚያስችለውን አሰራር እንዲያጸድቅ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡
በኮሎምበስ- ኦሃዮ በተካሔደው ምክክር የተሳተፉ ወገኖች በሰጡት አስተያዬትም አማራ ባንክ በክልሉ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው፤ በአክሲዮን ግዥውም እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከእራሳቸው አልፎ በክልሉ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠር እንደሚያስችል፤ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩትም ጥሩ የብድር አማራጭ እንደሚያቀርብ ነው የተናገሩት፡፡ የአንድ አክሲዮን መጠን አንድ ሺህ ብር ሆኖ ዝቅተኛ የአክሲዮን ብዛት ደግሞ 10 ዕጣ ማለትም 10 ሺህ ብር ነው። አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት መግዛት የሚችለው ከፍተኛ የአክሲዮን መጠንም 100 ሺህ ነው።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ አክሲዮን እንደተሸጠ፣ በዚህም 30 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን ከአደራጅ ኮሚቴው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ በህግ የተጠየቀውን 2 ቢሊዮን ብር በማስፈረም እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖችን ተሳትፎ በማረጋገጥ አማራ ባንክ ሥራ እንደሚጀምርም የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ- ከኮሎምበስ- ኦሀዮ